የአውሮፓ ህብረት (EU) ኮሚሽን፣ የቲክቶክ የይዘት ማቅረቢያ ስርዓት (Algorithm) በተለይም በታዳጊዎችና በወጣቶች የአእምሮ ጤና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው በሚል ኩባንያውን ከሷል።
ኮሚሽኑ እንደገለጸው፣ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ 189 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክቶክ፣ ተጠቃሚዎች ለተወሰኑ ይዘቶች “ፍላጎት የለኝም” (Not Interested) ቢሉም ተመሳሳይ ቪዲዮዎችን በተደጋጋሚ በማቅረብ ሊጎዷቸው ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል ስለ አካል ገጽታ፣ ራስን ማጥፋትና የአመጋገብ ችግሮች የሚያተኩሩ ይዘቶች ይገኙበታል። ይህም የተጠቃሚዎችን ጭንቀትና ድብርት ሊያባብስ እንደሚችል ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል።
የአውሮፓ ህብረት የቴክኖሎጂ ፖሊሲ ኃላፊ ሄና ቪርኩነን፣ የቲክቶክ አሰራር ተጠቃሚዎችን ከመተግበሪያው በቀላሉ መውጣት ወደማይችሉበት ተደጋጋሚ የአጠቃቀም አዙሪት ውስጥ እንደሚያስገባ ገልጸዋል። በተለይም የታዳጊዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ኩባንያው የአሰራር ስርዓቱን እንዲያሻሽል ጠይቀዋል።
ቲክቶክ በበኩሉ የቀረበበትን ክስ “መሠረተ ቢስና የተዛባ” በማለት ውድቅ አድርጓል። ኩባንያው ጎጂ ይዘቶችን የሚከለክል ፖሊሲ እንዳለውና ተጠቃሚዎች በመድረኩ ላይ የሚያዩትን ይዘት የመቆጣጠር አማራጮች እንዳሏቸው አስታውቋል።
በዲጂታል አገልግሎቶች ህግ (Digital Services Act) መሠረት የተጀመረው ምርመራ፣ ቲክቶክ ተጠቃሚዎችን ለረጅም ጊዜ በመተግበሪያው ላይ እንዲቆዩ የሚያደርገውን የንግድ አሰራር እና የ“ፎር ዩ” (For You) ገጽ አቀራረብ ላይ ያተኮረ ነው።
ቲክቶክ ከዚህ ቀደምም ከሱስ አስያዥ አሰራር ጋር በተያያዘ በተለይም ያልተገደበ የቪዲዮ ማሸብለል (Infinite Scroll) እና የማስታወቂያ ግልጽነት ጉድለት ላይ የህብረቱ ምርመራ ተደርጎበት ነበር። በአሁኑ ምርመራ ውጤት መሠረት ጥሰት እንዳለ ከተረጋገጠ፣ ኩባንያው እስከ ዓለም አቀፍ ዓመታዊ ገቢው 6 በመቶ የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ተገልጿል።
