Home ማኅበራዊ ጉዳይ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) እና አዝጋሚው የአፍሪካ የወል ገበያ ጉዞ!

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) እና አዝጋሚው የአፍሪካ የወል ገበያ ጉዞ!

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) እና አዝጋሚው የአፍሪካ የወል ገበያ ጉዞ!

አፍሪካ ውስጥ አንድ የወል ገበያን የመፍጠር እንቅስቃሴ ታሪክ የተጀመረው በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተቋቋመ በኋላ ነበር። ነጻ የወጡ አዳዲስ የአፍሪካ ሀገራትን አሰባስቦ የተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ውሕደትን የመፍጠር ትልም ነበረው። ይኽ ትልሙ ከዚህም አልፎ አንድ የጋራ ገበያና የጋራ የጉምሩክ ሥርዓትን ያቀናጀ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በመፍጠር አውሮፓን የመምሰል ዕቅድ የነበረው ጭምር ነበር። በ1980 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ይረዳ ዘንድ የአፍሪካ የጋራ ገበያ ምሥረታን ለማከናወን የሚያግዘውን የሌጎስ የድርጊት መርሃ ግብር አፀደቀ። በ1991 ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የጉምሩክ ማኅበር፣ አንድ የጋራ ገበያ እና የኢኮኖሚ/ገንዘብ አሃድ መመሥረትን ጨምሮ ባለ ስድስት እርከን ፍኖተ ካርታ የያዘውንና በጥቅሉ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብን (AEC) ለመመሥረት የሚረዳውን የአቡጃ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ኾኖም በ1957 የአውሮፓ ሕብረት በአህጉሩ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ይረዳ ዘንድ የመሠረተውን የሮም ስምምነት ተከትሎ በፍጥነት በመንቀሳቀስ፣ በ1968 የዓለም ትልቁን የጉምሩክ ሕብረት፣ በ1992 ደግሞ ትልቁን አንድ የዓለም ገበያ መፍጠር የቻለ ቢኾንም፤ የአፍሪካ መሪዎች ግን ኢኮኖሚያዊ የውሕደት ራዕያቸውን መሬት ላይ አውርደው የሠመረ ለማድረግ እና እድገት ለማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል። በ2002 የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመተካት ‹‹የአፍሪካ ሕብረት›› (AU) የተቋቋመውም ይኽንን የውሕደት አጀንዳ ተቋማዊ እና ፖለቲካዊ ተነሳሽነት ለመሥጠት ነበር። ይሁን እንጂ የአፍሪካ ሕብረት በተቋማዊ ቅርጹ ከአውሮፓ ሕብረት (EU) ጋር መሳ ለመሳ የሚታይ ቢመስልም፣ እንደ አውሮፓ ሕብረት የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውሕደት በፍጥነት ማሳደግ አልተቻለውም።

የአፍሪካን የውስጥ ንግድ ልውውጥ የሚዘውሩት ትላልቅ የንግድ ወጪዎች

ከፍ ብለን ባነሳነው ምክንያት፣ አውሮፓ በዓለም በኢኮኖሚ የተዋሐደ አህጉር መኾን ስትችል፣ አፍሪካ ግን የመጨረሻው ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይኽም የኾነው ከ80 በመቶ በላይ የሚኾነው የአፍሪካ ንግድ ከተቀረው ዓለም ጋር የሚከናወን በመኾኑና በአፍሪካ ውስጥ ያለው ንግድ ከጠቅላላው የንግድ ልውውጥ ከ14 በመቶ በላይ ድርሻ የሌለው በመኾኑ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን አውሮፓ ወደ 70 በመቶ የሚጠጋ ንግዱን፣ ሰሜን አሜሪካ 54 በመቶ የሚኾነው ንግዱን፣ እስያ 51 በመቶ እንዲሁም ላቲን አሜሪካ 15 በመቶው የሚኾነው ንግዳቸው አህጉር አቀፍ ነው። ምንም እንኳን የሌጎስ የድርጊት መርሃ ግብር እንደ ምዕራብ አፍሪካ መንግሥታት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ECOWAS)፣ እንደ ምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) እንዲሁም እንደ ደቡባዊው አፍሪካ (SADC) ያሉ በርካታ የቀጣና ኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችን (RECs) ለመፍጠር ቢችልም፣ በሁሉም የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች (RECs) ውስጥ ያለው ውሕደት ግን ጥልቀት የጎደለው እና መግባባትም ያነሰው ነው፡፡

እንዲህ ባለው የኢኮኖሚ ውሕደት ችግር ምክንያት አፍሪካ ከፍተኛ የንግድ ወጪ የሚጠይቅባት አህጉር ሆና ቆይታለች። ከፍተኛ የታሪፍ እንቅፋቶች (በአማካይ 8.7 በመቶ) እና በከፋ መልኩ ከታሪፍ ውጪ ያሉ ሌሎች እንቅፋቶች (ለአብነትም እንደ ከባድ የጉምሩክ አሠራሮች እና ከልክ ያለፈ ሕግና ደንቦች) በመላው አፍሪካ የንግድ ሥራን እጅግ አስቸጋሪ አድርገውታል። በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ የንግድ ልውውጦች መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች በማስፋፋት፣ አህጉሪቱ ለኢንዱስትሪ ልማት ለምትፈልጋቸው ኢንቨስትመንቶች እና ምጣኔ ሃብቶች ማነቆ በመኾን፣ ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ ኤክስፖርት የሚደረጉባቸውን መንገዶች በማብዛት እና ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶችን በማፋፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሳተፍ ሒደቱን አወሳስበውታል። መፍትሔው፣ በአህጉሪቱ የታሪፍ ነጻነት፣ የተመቻቸ የንግድ ሥርዓት እና ትስስርን በሚያመጣ ፖሊሲ ኢኮኖሚያዊ ውሕደት መፍጠር ነው። የአፍሪካ ልማት ባንክ በአንድ ወቅት በትዊተር ገፁ ላይ ‹‹ቀጣናዊ ውሕደት ለአፍሪካ ልማት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው›› ብሎ ማስነበቡ ለዚህ አባሪ ነው።

አሕጉራዊው ነጻ የንግድ ቀጣና፣ ጥልቅ ወደኾነ ውሕደት ለማምራት እንደ አንድ ጉልህ እርምጃ ይወሰዳል

ይኽንን ተግባር ለማሳለጥ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ሥር የመሠረተው ስምምነት በማርች 21 ቀን 2018 ፀድቆ፣ ግንቦት 30 ቀን 2019 ሥራ ላይ ውሏል። በወቅቱ 24 አገሮች ስምምነቱን በሀገራቸው ያጸደቁበትን ሰነድ ገቢ አድርገዋል። በሜይ 2022 ደግሞ 54 ሀገራት ስምምነቱን የፈረሙ ቢኾንም በሀገራቸው የመጨረሻ የሥልጣን አካል አጸድቀው ሰነዱን ገቢ ያረጉት ግን 46ቱ ሀገራት (85.2%) ናቸው።

ሒደቱን ወደፊት ለማራመድ፣ የአፍሪካ ሕብረት 12ኛው ልዩ ስብሰባውን በኒያሚ፣ ኒጀር ጁላይ 7 ቀን 2019 አካሔደ። ይኽን ተከትሎም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስምምነት መሠረት መደበኛው የንግድ ልውውጥ ጥር 1 ቀን 2021 በይፋ ተጀመረ።

በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ለአፍሪካ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያገኝ ነው። ለምሳሌ  በተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) ሪፖርት መሠረት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) በአፍሪካ አጠቃላይ የንግድ ልውውጥ ላይ 17.6 ቢሊዮን ዶላር (2.8 በመቶ) በመጨመር ኤክስፖርትን በ25.4 ቢሊዮን ዶላር (ወይም 4 በመቶ) እንደሚያሳድግ ተመላክቷል። ስምምነቱ የአህጉሩን ንግድ ከታሪፍ ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን 85 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ ንግድ እንዲከናወን በማድረግ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን የንግድ ልውውጥ በ34.6 ቢሊዮን ዶላር (52 በመቶ) ለማሳደግ ይረዳል።

አፍሬክሲምባንክ ባደረገው ጥናት ደግሞ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) የገበያ መረጃ እንዲጋራ እና በአፍሪካ ሀገራት ዘንድም በስፋት እንዲሰራጭ በማድረግ በአፍሪካ ውስጥ ያለው የንግድ ልውውጥ ወደ 400 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ይገልጻል። ከዚህም በላይ ደግሞ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስምምነት መሣካት በስፋት የሚታየውን የአፍሪካን መደበኛ ያልሆነ የንግድ ልውውጥ ወደ መደበኛው ዘርፍ ለማምጣት እና የቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለት እድገትን ለማገዝ ይረዳል። ከዚህም ባሻገር አፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እና የ1.2 ቢሊየን ሕዝቧን 3.4 ትሪሊየን ዶላር አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሰባሰብ ጉልህ የሆነ የመደራደር አቅም እንዲኖራትም ያስችላል።

ኾኖም፣ ይኽ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስኬት በበርካታ መሰናክሎችም የታጀበ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሀገራቱ ለመወሰን ያለባቸው የፖለቲካ ፍላጎት እጦት ነው። ለምሳሌ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስምምነት አሁን ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በ49 ሀገራት በመርኅ ደረጃ የተፈረመ ቢሆንም፣ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስፈልገው የማጽደቂያ ሰነድ ገቢ ያደረጉት ሀገራት ቁጥር ግን ያን ያህል አይደለም። ስምምነቱን ወደ መሬት ለማውረድ ቢያንስ በ22 ሀገራት ዘንድ መጽደቅ ይኖርበታል። ምንም እንኳን ስምምነቱ በጥር ወር ተግባራዊ መሆን የነበረበት ቢሆንም እስካሁን በሥራ ላይ ለማዋል በሀገራቸው ያጸደቁ ሀገራት ቁጥር ግን 14 ብቻ ነው። በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ያለውን ይኽን አዝጋሚ የማጽደቅ ሂደት ግምት ውስጥ በማስገባት የተቀሩት ሀገራትም ማጽደቃቸውን የማረጋገጡ ሥራ እስከዚህ ዓመት መጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአፍሪካ ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ናይጄሪያ ይኽንን ስምምነት አለመፈረሟን መግለጽ ያስፈልጋል። ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ‹‹ችግሩን ለመፍታት የአጭር፣ መካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እርምጃዎችን እንዲዘጋጅ›› ለባለድርሻ ኮሚቴ ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ ቢኾንም፣ የኮሚቴውን ውጤት ከተመለከቱ በኋላ ስምምነቱን ስለመፈረማቸው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

ይኽ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስምምነት የተሰጠው የተበታተነ ምላሽ በአፍሪካ የነፃ ንግድ ገበያ የመፍጠርም ኾነ ነጻ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ራዕይ አስመልክቶ ያለውን ልዩነት በግልጽ ያንፀባረቀ ነው። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) እውን ይኾን ዘንድ እጅግ የሚሹት እንደ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ እና ጋና ያሉ በአህጉሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚ እያደጉ ያሉ ሀገራት ሲሆኑ፣ ሌሎች እንደ ናይጄሪያ ያሉ ሀገራት ደግሞ ሌሎችን የመጠበቅ እና የማመንታት ባሕሪዎች ይታይባቸዋል። ምንም እንኳን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) በአፍሪካ ሀገራት መካከል እስከ 90 በመቶ በሚሆኑ ሸቀጦች ላይ የታሪፍ እንቅፋቶችን ያስወግዳል ተብሎ ቢጠበቅም ስምምነቱ ወሳኝ ለኾኑ ምርቶች፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ምርቶች እና ለሌሎችም የተሟላ አሠራር አለው፡፡ ይኽ የጋራ ገበያ የመፈጠር ውጥን አንዴ ከተሳካ፣ እንዲሁ በቀላሉ ሊቆም የማይችል ከመኾኑም በላይ ለንግዱ ዓለም ሌሎች አማራጮችም ወሳኝ መሠረት ሊሆን ይችላል።

ከፍ ብለን ካነሳነውም ባሻገር፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) በተቋማትና በአቅም ጉድለቶች ምክንያት በአፈጻጸም ተግዳሮቶችም ሊደናቀፍ ይችላል። ይህ ችግር በብዙ የአፍሪካ አገሮች የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (REC) እና የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) ስምምነቶች ደካማ አፈጻጸም ላይ በግልጽ የታየ ነው። በጄኔቫ ዩኒቨርሲቲ ኢምሪተስ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄይም ደ ሜሎ በአፍሪካ ቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (REC) ላይ ባደረጉት ጥናት የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችን (RECs) ውሕደት ጥልቀት የሌለው መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም አልፈው ‹‹የንግድ እንቅፋቶችን በመፍታት የቀጣናዊ የንግድ ወጪዎችን መቀነስ በአፍሪካ ቀጣና የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ውስጥ ስኬታማ ውሕደት ለመፍጠር ፈተና ሆኖ ይቆያል›› ብለዋል፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታ፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) መሠረታዊ የአሠራር መሥፈርቶችን ቀርቶ አስፈላጊ ግዴታዎችን እንኳ አያሟሉም። የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች (REC) እና የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) በተመሳሳይ የትግበራ መሥፈርቶች ሊኖሩት ይችላል።

አፍሪካ፣ አህጉራዊውን ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ተግባራዊ ማድረግ አለባት

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ብዙ የአገር ውስጥ ፖሊሲና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ስለሚፈልግ፣ ብሎም ተዓማኒነት ያለው የአፍሪካ የጋራ ገበያና የጉምሩክ አሃድ ሊሆን ስለሚችል በነባሩ የአሠራር ሒደት ላይ ለውጥ ሊፈጥር ይችላል። ይሁን እንጂ፣ የአፍሪካ መሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች እየሔዱበት ያለውን በዝግታ እና ጥንቃቄ የተሞላበት የኢኮኖሚ ውሕደት ስናስብ፣ ይህ እውን ይኾን ዘንድ የፖለቲካ ፍላጎቱ እስካሁን ድረስ ማነቆ መኾኑን መረዳት አይከብድም፡፡ ኾኖም የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ አንድ ገበያ ፈጥሮ ከትልቁ የዓለም ጋር ከመዋሐድ ውጪ ሊኾን አይችልም፡፡ ለዚህ ደግሞ አፍሪካ ከሁሉም በፊት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) መሬት ላይ እንዲወርድ ማድረግ ይኖርባታል።