የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው የኢራን ጦርነት ካልቆመ እና የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ ከቀጠለ የዓለም ምጣኔ ኃብት የመንኮታኮት አደጋ እንደተጋረጠበት አስጠነቀቀ።
አይኤምኤፍ የኢራን ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ ከፍተኛ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የምግብ ዋጋ ጭማሪ ስለሚታይ የዓለም ምጣኔ ኃብት እድገት ዝቅ እንዲል ያስገድዳል ሲል ገልጿል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የዓለም ምጣኔ ኃብትን በተነበየበት ሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው፣ የነዳጅ፣ የጋዝ እና የምግብ ዋጋ እየጨመረ የሚቀጥል ከሆነ እአአ በ2026 የዓለም ምጣኔ ኃብት እድገት ከ2 በመቶ በታች ሊሆን ይችላል ብሏል።
“ይህ ማለት ዓለም እአአ ከ1980 ወዲህ አራት ጊዜ ብቻ ወደ ተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ እየሄደች ነው ማለት ነው” ሲል ድርጅቱ ገልጿል።ዓለም በቅርብ ጊዜ የኢኮኖሚ ቀውስ ያጋጠማት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጊዜ ነው።
የኢራን ጦርነት ከጀመረበት ከስድስት ሳምንታት ወዲህ ዋናው የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እንዲሁም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው የሰላም ድርድር ያለውጤት በመጠናቀቁ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት “በድጋሚ የዓለም ኢኮኖሚ ከመስመሩ ውጪ የመሆን አደጋ ተጋርጦበታል፤ በዚህ ወቅት በየካቲት 2018 ዓ.ም. በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በመቀስቀሱ ነው።”በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያስከትሉ ከሚችሉት እጅግ አስከፊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የሆነው የነዳጅ ዋጋ መጨመር በዚህ ኣመት ታይቷል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ አንድ በርሜል የነዳጅ ዘይት በአማካይ 110 ዶላር ደርሷል።እአአ በ2027 ደግሞ 125 ዶላር እንደሚደርስ ተገምቷል።በእነዚህ ግምቶች ላይ በመመስረት አይኤምኤፍ በሚቀጥለው ዓመት የዋጋ ግሽበት እስከ 6 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።
ይህ ደግሞ ብሔራዊ ባንኮች የዋጋ ጭማሪን ፍጥነት ለመቀነስ የወለድ ተመኖችን ከፍ እንዲያደርጉ ሊያስገድዳቸው ይችላል።በኢራን ግጭት ወቅት የነዳጅ ዋጋ ወደ 120 ዶላር ከፍ ብሎ የነበረ ቢሆንም ማክሰኞ ዕለት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ 98.85 ዶላር ተሸጧል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ግጭቱ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከተፈታ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚወጣው የነዳጅ ምርት እና የውጭ ንግድ በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ መደበኛ መሆን ከጀመረ በ2026 የዓለም እድገት በ3.1 በመቶ ብቻ እንደሚቀንስ ግምቱን አስቀምጧል።
BBC
