የቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዓለማቀፍ ቅርስ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ “ለታሪክ ግድ የሌላቸውና ችኩል አካላት” ታሪካዊውን የቅዱስ ላሊበላ አካባባቢን ማኅበረሰብ “ከልመና” ተግባር ጋር በማያያዝ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ተነቀሳቃሽ ምስል አጋርተዋል ሲል ከሠሠ።
ቤት ለቤት እየዞሩ በዘፈን መልክ በልመና ለሚተዳደሩ “አባ ውዴ” ወይም “ሃሚና” ለተባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቅዱስ ላሊበላን ስም መስጠት “አሳፋሪ”፣ “የድንቁርና” እና “የታሪክ ፍልሠትን” የሚያስከትል ድርጊት ነው ሲል ጽሐፈት ቤቱ ወቅሷል።
ይህ ድርጊት በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል መኾኑ ሊታወቅ ይገባል ያለው ጽሕፈት ቤቱ፣ አርቲስቶችና አዝማሪዎች ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ የስፍራውን ስም ካልዋለበት በማዋል የታሪክ መዛባት ለመፍጠር እየሞከሩ ይገኛሉ ሲል ወቅሷል።
ጽሕፈት ቤቱ፣ በልመና የተሠማሩ ወገኖች ከላሊበላ አካባቢ ሕዝብ ባሕልና ስነ ልቦና ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም ብሏል። በስም ማጥፋት ላይ የተሠማሩ አካላት ባስቸኳይ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ለስም ማጠልሸት ድርጊታቸው ይቅርታ እንዲጠይቁ ጽሕፈት ቤቱ ጠይቋል።
