የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር ባደረጉት ጥረት የኤንሪኮ ማቴይ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ሽልማቱ ሜሎኒ በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል ያለውን የጂኦፖለቲካዊ ትብብር ለማሳደግ፣ እንዲሁም በጣሊያንና በአፍሪካ ሀገራት መካከል አዲስ የትብብር አቅጣጫ ለመፍጠር ባቀረቡት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ምክንያት መሰጠቱ ተገልጿል።
ሜሎኒ በአፍሪካ አህጉር የኢኮኖሚ እድገትን ለማበረታታት፣ ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከርና ጣሊያን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስፋት በሚያደርጉት ጥረት ሽልማቱን እንዳገኙ ዘገባው ያመለክታል።
ጣሊያን በአፍሪካ ለመተግበር ያቀደችው የማቴይ ዕቅድ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ትብብር ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል። ዕቅዱ በኢኮኖሚ፣ በልማትና በሌሎች የትብብር ዘርፎች ግንኙነቶችን ለማስፋት የሚያተኩር ነው።
የኤንሪኮ ማቴይ ሽልማትም በጣሊያንና በአፍሪካ መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉና ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚያጠናክሩ ጥረቶችን ለማበረታታት የሚሰጥ ሽልማት መሆኑ ተጠቁሟል።
