ተመስገን ኡካሬ (የሐጌ ልጅ)
ድምፃዊ፣ የፒያኖ እና የኪቦርድ ተጫዋች አለማየሁ ሂርጶ፣ ከሙዚቃ ጋር ቁርኝነታቸው የሚጀምረው ከብላቴናነት ዘመኑ ነው፡፡ የሙዚቃ ጅማሮውን ያደረገው በአዲስ አበባ ዓለም ገና አካባቢ ኬንቴር በተባለ ልዩ ቦታ ነው፡፡ እዛው በነበረው ተሳትፎ በኪነጥበቡ ዘርፍ በይበልጥ በማደጉ እና የተሻለ ቦታ ለመስራት ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ መሰልጠን ጀመረ፡፡ በመርካቶ ከፍተኛ አምስት በተባለ ቦታ እዛው ብዙ ነገሮች አይቷል ፤ የሙዚቃን ምንነት ከሌሎች እውቅ ሙዚቀኞች ልምድ ወስዶ በጣም በመብሰል እውቀትን ቀስሟል፡፡
ድምፃዊ አለማየሁ ሂርጶ ከከፍተኛ አምስት መርካቶ በነበረው ቆይታ ብዙ ልምድ በማካበቱ ወደ ተለያየዩ ክለብ ቤቶች በመግባት ሙዚቃዎችን በመጫወት ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ የመጀመርያ “ሀ” ብሎ ሙዚቃ የሰራውና ወደ ሕዝብ ያደረሰው “ሻላላ” የተሰኘ ሙዚቃው ከቱሼ በጋር በመሆን ነበር ያወጡት፡፡ ይህ ሙዚቃ እንዲህ ይላል ስንኙ “ስትመላለሺ በአካላቴ ክፍል ፣ አይሆንም ወዳጄ የደላሽ ይመስል”፡፡
በመቀጠል ወደ ራሱ ሙዚቃ በመምጣት ሆድዬ፣ ተመቸሽ ወይ፣ በፈገግታሽ፣… የተለያዩ ነጠላ ዜማዎች ሰርቷል፡፡ ሌሎች ድምፃዊያኖች የሰሩትን ሙዚቃ እንደ አዳዲስ በመጫወት በራስ ቀለም ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል የሙሉጌታ ቅንብር የኾነውን የሰይፉ ዮሐንስ (በመልክሽ አይደለም) ሙዚቃ እና የመሳሰሉትን ሙዚቃዎች ተጫውቷል፡፡
ሙዚቃዎችን ማምረት የሚያውቅበት ድምፃዊ አለማየሁ ሂርጶ የተለያዩ ድምፃዊያን የዘፈኑበት ቴክ ፋይፍ (5) አምስቶቹ በመስራት ወደ ዝና እየተንደረደረ በይበልጥ ግን ዘመን እና ሁኔታዎች የማይለውጡት ለምርምር ለሚጋብዝ የኤልያስ መልካ የሙዚቃ አመለካከት እና ጥራት የተለካበት፡፡
የጥምረት ህያው ምስክርነት ጎሳዬ ተስፋዬ እና አለማየሁ ሂርጶ(ኢቫንጋዲ) አልበም ይዘው መጡ፡፡ በዛው ውስጥ አለማየሁ ሂርጶ ከመጣባቸው የሙዚቃ መንገድ የሚለይ ከሕይወቱ መስመር ጋር የተገናኘ ትንቢት መሰል ሙዚቃ አወጣ “ባይተዋር”፣ “ዴዝዴሞና”፣ “ያስብሻል”፣ “ለበጎነው” ሙዚቃዎችን ሠራ፡፡ ስለ ሙዚቃ ስንኞች ልንገራችሁ፡፡
- ‹‹ዴዝዴሞና›› የተሰኘውን በመፅሐፍ የተፃፈ በቲያትር መልክ የተተወነን ታሪክ ወደ ሙዚቃ ተቀይሮ በአለማየሁ ሂርጶ ጉሮሮ ተዚሟል፡፡ መፅሐፉን የፃፈው ዊልያም ሼክ ስፒር የተረጎመው ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ወደ ትወና ቀይሮ አምጥቶታል፡፡
“እንግዲህ ይንቆርቆር እንባ ከትራሴ
የኦቴሎን ታሪክ ደገምኩት በራሴ
እንደ እሱ ጨክኜ ባላጠፋ ነፍስ
ኦቴሎን ሆኛለሁ ከንቱ ልበ ቢስ
በሌላ አትይብኝ ብወድሽ ነው እና
ይቅር በይኝ ባክሽ ዴዝዴሞና”
ግጥም መሰለ ጌታሁን ፤ ዜማ ደረጀ ተኮላ ፤ ቅንብር ኤልያስ መልካ፡፡- ባይተዋር- ከእውነተኛ አለም የተቀዳ የማይፋቅ ታሪክ ከህምም እና ከሲቃ ጋር የተቆራኘ፡፡ አለማየሁ ደመቀ በዚህ ሙዚቃ ዙርያ ሲናገር “በወቅቱ አለማየሁ ሂርጶ ባለቤቱ በሕይወት ያጣበት ነበር፡፡ እኔም በተመሳሳይ እናቴን ያጣሁበት ነበር” ይላል፡፡ ብቻውን አንድ ቢሮ ውስጥ በመሸሸግ ብዕር፣ የአእምሮ እምቅ እና ወረቀቱን ከእንባ ጋር አርሶ የፃፈው እውነታን ጣርያ የነካበት ፅሁፍ ነበር፡፡ ልክ ግጥሙን ፅፎ ለአሌክስ ሲሰጠው በእንባ ተጠመቁ ፤ ያኔ ዘፈኑ ልክ መጣ፡፡
“አልለይም አለኝ ቀን ለሊቱ
ስቃይ ሆኖብኛል መለየቱ
አቤት መከራ አቤት ጭንቀቱ- ጭር ያለው ቤቴን ባየሽው እቱ”
እንባ ብቻ ነው የኔስ ጓደኛ
የማይለየኝ ስሄድ ስተኛ”
ግጥም እና ዜማ አለማየሁ ደመቀ ፤ ቅንብር ኤልያስ መልካ
በዚህ ሙዚቃዎች በባሕር ማዶ አውሮፖ የተለያዩ ሀገራት መዘዋወር እውቅና እና ዝናን አተረፈ፡፡ በሚመላለስበት ወቅት ህመም አጋጥሞት ረዥም ዓመታት በሕክምና እና በስቃይ ቆይቷል፡፡
ዘፈኖቹን ኾኖ እውነታውን ምድር ላይ የተወነው አሌክስ…
ሕይወት ውጣ ወረድዋ ብዙ አድካሚነቷ አንዱን ሞላው ስትል ደግሞ አንዱ ይጎላል፡፡ ከፍታ እና ዝቅታ አንዱ የፈተና መድረኮች ናቸው፡፡ ካለፍናቸው ጀግና ልባም በዛ ላይ ብቁ አስተዋይ በሁሉም ነገር የደነደነ የመሸከም ጫንቃ ይሰጥሀል፡፡ የመሻገርያ ቁልፎችን ፍለጋ ስትዳክር በመጨረሻም ሲገኙ ያነቁሀል፡፡
ከአለማየሁ ሂርጶ ላይ ያንን ተመልክተናል፤ ያለፈበትን ሕይወት ሕመም ሲያወጋው እጅግ በተሰበረ ልብ ነው …ሀገሩን እያሰበ ያንን ጭንቀት ጊዜ ወደ ኋላ ተስቦ አይቶ በሆድ ይፍጀው ስሜት “ማን እንደ ሀገር” ሲል ተደጋጋሚ ጊዜ ይገልፃል፡፡
ይንን ስሰማ ባይተዋር የተሰኘ ሙዚቃ ድቅን ይልብናል፡፡ አለማየሁ ደመቀ ይንን ሕይወት ውጣ ውረድ ቀድሞ አስቦ ነው የሰጠው ብለን እንገረማለን ፤ ምክንያቱም ሕመሞቹ በሙሉ ሙዚቃውን ይወክላል፡፡
የዛሬ 19 (ዐሥራ ዘጠኝ) ዓመት እጅግ ዝነኛ የነበረ ሰው ከሀገር ውጪ ለሙዚቃ ሥራ ወደ ባህር ማዶ ሲሄድ ህመም አጋጥሞት ከህመሙ ጋር እየታገለ እና በተለያዩ ምክንያት ለ19 ዓመት ድረስ ቆየ ፤ በሕመም እና በናፍቆት ሲሰቃይም ቆየ፡፡ የናፍቆት መውጫው የሕመሙ ሲቃ መገለጫ ሙዚቃ ናት ፤ ከፒያኖ እና ከኪቦርዱ የሙዚቃ መሳርያ ጋር በተዘጋ ቤት ያወራሉ፡፡
ቆዳው ጠንክሮ የመጣው አሌክስ…
ከሞት ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው ችግር ፈተና ሁሉን አሳልፎ ስለ መጣ ምን ያህል አንዳች ነገር ቢገጥመው ነው የመቻል አቅሙ የበረታው አጠንክሮት ከፍታ ላይ ያስቀመጠው፡፡ ለብዙዎች ተምሳሌት የሚሆን አንድ የዓለም ውበቷ ይህም አይደል፡፡ በችግር ቀርፃ ትሸልምሀለች በመታሸት ውስጥ ብዙ የምታፀዳው እና ብልህነት የምታገኘሁ ሌላ የሕይወት ገፅ አለ ፤ ያንን ገፅ አሌክስ ኖሮታል ፤ ተውኖታል፡፡
ነፃ-ነት ፈላጊው አሌክስ…
በፊት የጨዋታ ማዕበል የነበረው ኤሌክሶ በባህር ማዶ ባጋጠመው ህመም ብዙ ነገሩን አደብዝዞታል፡፡ አንድም እስር ቤት ለብቻው ተደርጎ መታሰሩ ነፃነት የተባለው እውነታ አሳጥቶታል፡፡ ነፃነት ናፋቂም አድርጎታል፡፡ ለብቻ ሲሆን ዝምታ ይሰፍናል፤ ከማንም ጋር አያወራም …በዛ ውስጥ በፊት የሚያውቀው ሰው ጋር ተከቦ መኖር ያለውን ስሜት ሙሉ በሙሉ ቀምቶታል፡፡ ይህ ሁሉም ሰው የሚመኛት የሚሻማባት “ነፃነት” የተባለው ትርጉም ለማጣጣም ወደ ሀገሩ ተመልሷል፡፡
ትዝታ አዋቂው አሌክስ…
እያንዳንዷን ድርጊት አንድም ሳትቀር ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያንን ናፋቂ ዘመን ያስታውሳል፡፡ አብረውት የሰሩት በሕይወት ያሉ እና የሌሉትን አንጋፋ የሙዚቃ ከያኒያኖችን እያስታወሰ ከሳቁም ከቁም ነገሩም ይነግረናል፡፡ በጣም የሚያስገርመው ድምፃዊ ታደለ ሮባን ደግነትን የተናገረበት አጋጣሚ ነው፡፡
“እኔ እና ታደለ ሮባ አንድ ቤት እንኖር ነበር፡፡ እኔ ስታመም በዛን ጊዜ የቆጠበውን አንድ ሺህ ብር አውጥቶ አሳክሞኛል” ሲል ከታደለ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት አንስቷል፡፡
ዳግመ ጎሳዬ ተስፋዬ እና አለማየሁ ሂርጶ…
የአንድ ሳንቲም ሁሉት ገፅታዎች፣ ወዳጅነታቸው በሙዚቃ አልበሞች ወይም በማይክ ላይ ባላቸው ቆይታ ብቻ አይደለም፡፡ አብረው በቆዩ ጊዜያት ሙሉ የሕይወትን ፈተና ቀምሰዋል፣ የማጣትን የማግኘትን፣ የትጋት ተምሳሌት፣ አንዱ ከአንዱ ጋር ውህድ ፈጥሮ ማዜም፣ ተምሳሌት፣ ለትውልድ አትራፊ የሆኑ ሥራዎች ማበርከትን፡፡ ከብዙዎች ለጥቂቶች ሚታደሉትን ስጦታ የተሸከሙ ናቸው፡፡
ያንን አይረሴ የዘመን ሐውልት የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ለመድገም “ሞያ በልብ ነው” ብለዋል፡፡ አብሮ ብዙ የተሻገረ ሰው እንኳን በዚህ ቋንቋ አይደለም በዓይን ጥቅሻ ሁላ ይግባባሉ ወደ ፊት ለዚህኛው ትውልድ ምን ያሳዩን ይሁን? በጉጉት የምንጠብቅ ይሆናል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 225 ግንቦት 2017 ዓ.ም
