ግዮን መጽሔት :- በተሰናበትነው 2018 ዓ.ም እንደ ግለሰብ፣ እንደ ማኅበረሰብ፣ ብሎም እንደ ሀገር ያገኘነውም ያጣነውም ብዙ ነው፡፡ መጽሔታችን ግዮን ባለፉት ዓመታት ስታደርግ እንደቆየችውም በዓመቱ በሀገራችን ወሳኝ ከምንላቸው ኹነቶችና ክስተቶች ጎን ለጎን በአጭርም ይኹን በረጅም የሕይወት ዘመናቸው ለሀገራቸው ታላላቅ አስተዋጽዖዎችን አበርክተው በዕረፍተ ዘመን የተገቱ ታላላቅ ስብዕናዎች ትዘክራለች፡፡ በዚህ ዓምድም ሃገራቸውን በልዩ ልዩ የሙያ መስኮች አገልግለው በ2014 ዓ.ም ያረፉ ኢትዮጵያውያንን እንደሚከተለው በአጭር በአጭሩ እናስታውሳለን፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከአባታቸው አቶ ኢድሪስ ዘለቀ እና ከእናታቸው ወ/ሮ መነን ሽፋው፣ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1924 በወሎ ቦረና ገነቴ አካባቢ ልዩ ስሙ “ዳሎታ” በተባለ መንደር ተወለዱ፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ – በ1966 በመሠረቱት የትዳር ዓለም ከባለቤታቸው ወ/ሮ ሐሊማ ሸህ ዐብዲልጀሊል ጋር ዘጠኝ ልጆችን ያፈሩ ሲኾን፣ እልፍ አዕላፍ ዓሊሞችንና ደረሳዎችን እንዲሁም የዕውቀት ማዕከላትን መተካት ችለዋል፡፡ ከ2011-2014 የኢትዮጵያ የእስ/ጉ/ጠ/ም/ቤት ፕሬዝደንት
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በእግራቸው ተጉዘው ያከናዎኑትን ጨምሮ አርባ ጊዜ የሐጂ ሥነ ስርዓት አከናውነዋል፡፡ እስከ መስከረም 2018 ድረስ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ መንፈሳዊ ንቃታቸው እና ጤንነታቸው እጅግም የተሟላ ነበር፡፡
ከሳምንቶች በፊት በአጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ ዕለተ ዕሁድ ጥቅምት 09 ቀን 2018 ከዚህ ዓለም አርፈዋል፡፡ አላህ የጀነት ያድርጋቸው። ህዝበ ሙስሊሙም አርአያዊ ትውፊታቸውን ያስቀጥል። የሐገር መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ሙፍቲና መሰሎቻቸው የደከሙለትን ሰው ተኮር እሴት የዘዎትር መመሪያ አድርገው መንፈሳዊ መሪያችንን ያስታውሱልን።
የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም በሚሌኒየም አዳራሽ ብሔራዊ የሽኝት ሥኘ ሥርዓት ትልልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በታደሙበት ከተከናወነ በኋላ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ተፈጽሟል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም (ሊቀ ጳጳስ)
ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ሊቀ ጳጳስ በ1950 ዓ/ም ኦርቶዶክሳውያን ከሆኑና ፈሪሃ እግዚአብሔር ካላቸው ከእናታቸው ከወ/ሮ አስካለማርያም ማናየ እና ከአባታቸው ከአቶ ባሳዝነው ወንድምአገኘሁ በሚያዚያ ወር በቀድሞው የሸዋ ክፍለ ሀገር መርሐ ቤቴ አውራጃ በአሁኑ የሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ በሚገኘው ልዩ ስሙ በላይ ኸያዱር በዓለ ወልድ በሚባለው ቀበሌ ተወለዱ፡፡
በትሩፋት የከበረው መንፈሳዊ ሕይወታቸውና ብቃታቸው ተመዝኖ ሐምሌ 9 ቀን 1997 ዓ.ም. በተደረገው የኤጲስቆጶሳት ምርጫ በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አሳሳቢነት በመንፈስ ቅዱስ ተመርጠው ነሐሴ 22/1997 ዓ/ም የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ አንብሮተ ዕድ ተሹመዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ከግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመድበው ገዳማትን ለማጠናከርና ችግሮቻቸውንም ለመፍታት ሰፊ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ ለመግባት በጥናትና በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡
ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ባደረባቸው ሕመም በጸሎት፣ በጸበልና በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 18 ቀን 2018 ዓ/ም በተወለዱ በ68 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ማያልፈው ዓለም ተሻግረዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም ጥር 19 ቀን 2018 ዓ/ም በታላቁ ደብረ ሊባኖስ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በክብር ተፈጽሟል፡፡
አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ
አዲስ አበባ ኡራኤል አካባቢ በ1975 ዓ.ም ተወልዶ ያደገው ነጻነት ወርቅነህ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ የሕይወት ጥሪውን ለይቶ በማወቅ ለሚወደው የትያትር እና ጥበብ ራሱን የሰጠ እና በዚህም ለከፍተኛ ደረጃ የደረሰ አርቲስት ነበር፡፡ ተዋናይ፣ ኮሜዲያን፣ የቴሌቭዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ በኢትዮጵያ የፊልም እና የቴሌቭዥን ታሪክ ውስጥ የራሱን ልዩ የሆነ የአቀራረብ ስልት እና የትወና ጥበብ በማሳየት የሚታወቅ ባለሙያ ነበር፡፡
ለቅርብ ወዳጆቹ ደጋግሞ የሚናገረው አንድ ልብ የሚነካ ኑዛዜ ነበረው፦ “ስሞት ከአያቴ አጠገብ አሌልቱ ጊዮርጊስ ቅበሩኝ” የሚል፡፡ ይህ ምኞቱ ከአፈር በታችም ቢሆን አብሯቸው የመሆን ጉጉቱን የሚያሳይ ነበር። የሚገርመውና ልብን የሚሰብረው ግን፣ ነፃነት ከመሞቱ ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ አሌልቱ ጊዮርጊስ ተጉዞ ቤተክርስቲያኑን ስለማደስና ስለ ልማት ስራዎች ሲመክር መቆየቱ ነው። ሞት በደጃፉ እንዳለ ሳያውቅ፣ ለአያቱ ጓሮና ለዘላለም እረፍቱ ሲዘጋጅ የቆየ ይመስላል። ሆኖም የሀገር ዕዳና የጥበብ ባለቤት በመሆኑ፣ ኑዛዜው ሳይፈጸም የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በታላቁ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ነፃነት ወርቅነህ፣ ከንፁህ ዘር በላይ ጋር ትዳር የመሠረተ ሲሆን የሦስት ልጆች አባት ነው። ነፃነት ወርቅነህ ጥር 8 ቀን 2018 ዓ.ም 44 ዓመቱን ሊይዝ 30 ቀናት ሲቀረው ከዚህ አለም ድካም አርፏል፡፡ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱም እሁድ፣ ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
አማን ፍስሐጽዮን
አቶ አማን ሐምሌ 3 ቀን 1964 ዓ.ም ከአባቱ ከአቶ ፍስሐ ጽዮን ገብረ ሕይወትና ከእናቱ ከወይዘሮ ሕይወት ተኬ በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ። ለቤተሰቡ ስድስተኛና የመጨረሻ ልጅ የሆኑት አቶ አማን እምነትን ማዕከል ባደረገ የቤተሰብ እሴቶች በነበረበት ቤት ውስጥ በወላጆቹ በአያቱ በወይዘሮ ይመስገን ገብረሥላሴ በማይነጥፍ ፍቅርና ምክር ታንጸው አድገዋል።
አቶ አማን በ2000 ዓ.ም ከአጋሮቻቸው ከአቶ ሙሴ ፍስሐጽዮን፣ አቶ ዮሃን ፍስሐ ጽዮንና አቶ ነቢዩ ያሬድ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስን (EBS TV) በሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ መሰረቱ።
አቶ አማንና የሕይወት አጋሩ ወይዘሮ ማክዳ አሰፋ የተገናኙበት 1989 ዓ.ም ሲሆን ከሁለት ዓመታት በኋላ ሚያዝያ 1 ቀን 1991 ዓ.ም በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል። ትዳራቸውም በጥልቅ ፍቅር ማደናቀፍ መደጋገፍ ሁኔታዎችና ፈተና በማይበግረው ጽኑ ታማኝነት ላይ የተገነባ የሕይወት ጥምረት ነበር። በዚህም ጊዜ አማኑኤል መቅደላዊትና ሰላም ፍስሐ ጽዮን የተባሉ ሦስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ኖቫ የተባለች የልጅ ልጅ ለማየትም በቅተዋል።
አቶ አማን ፍስሐጽዮን የካቲት 3 ቀን 2018 ዓ.ም በተወለዱ በ53 ዓመታቸው በአሜሪካን አገር በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። በዓድዋ ሙዚየም በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎችና ታዳሚያን በተገኙበት የሽኝት ፕሮግራም ከተከናወነ በኋላ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በጴጥሮስ ወጳውሎስ ተፈጽሟል፡፡
መምህር ዘለዓለም ወንድሙ
መምህር ዘላለም ወንድሙ (ስመ ጥምቀቱ ወልደ ሰማዕት) ከአባታቸው ከአቶ ወንድሙ ተማም እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ትክክልወርቅ ገብረኢየሱስ ነሐሴ 17 ቀን 1969 ዓ.ም በታሪካዊቷ ደብረ ሲና ከተማ ተወለደ፡፡ ገና በለጋነቱ የቤተክርስቲያንን ጠረን እየሳበ፣ በየኔት ለቋንቋ ተናጋሪዎች የሰጠው ትኩረት፡ በ2003 ዓ.ም ከ38 ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የተውጣጡ ደቀ መዛሙርትን አምጥቶ፣ ወጪያቸውን ሸፍኖ ካሰለጠነ በኋላ ወደየአካባቢያቸው እንዲያገለግሉ ልኮአቸዋል። በጸጨማሪም ለ57 ዓይነ ስውራን በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ከማድረጉ በተጨማሪ ለዘለቄታው ራሳቸውን የሚችሉበት ቦታ በመግዛት እንቅስቃሴ አስጀምሯል፡፡
በምሁር ኢየሱስ ገዳም 12 ልጆችን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ በማስመጣት ዲቁና እንዲማሩና ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው እንዲያገለግሉ አድርጓል፡፡ መምህር ዘላለም ወንድሙ ስመ ጥምቀቱ ወልደ ሰማዕት ለአገልግሎት በሄዱበት በሀገረ አሜሪካ በገጠማቸው ድንገተኛ ሕመም የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በተወለዱ በ49 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፏል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓቱም በመስቀል ዐደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ አማኞችና ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት የሥንብት መርኃ ግብር ተከናውኖ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ተፈጽሟል፡፡
ስለሺ መንገሻ
ጓድ ስለሺ መንገሻ ከዛሬ ሰማንያ አራት ዓመታት በፊት ነበር የተወለደው፡፡ በቀድሞ አርሲ ክፍለ ሃገር፣ ሶዴ በሚባል ወረዳ፣ ‹‹ሃሰን ዳቦ›› ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ በምትገኝ አንዲት የገጠር መንደር፡፡ እና እሱ በወርሃ ኅዳር ሦስተኛ ቀን 1934 ዓ.ም ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡የወላጅ አባቱ የባሻ መንገሻ መቼአምኜህ የአብራክና የእናቱ የወይዘሮ ደማ አለሚ የማኅፀን ፍሬ ሆኖ፡፡ ዳኸ፡፡ አደገ፡፡ ተመነደገ፡፡
ጓድ ስለሺ መንገሻ ከ1971 እስከ 1980 ዓ.ም በነበሩት ጊዜያት ውስጥ የአርሲ ክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ፣ የክፍለ ሃገሩ የኢሠፓአኮ 1ኛ ጸሐፊና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፤ እንዲሁም የአርሲ ክፍለ ሃገር ዋና አስተዳዳሪና በኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የክፍለ ሃገሩ አንደኛ ፀሐፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡ ከ1980 እስከ 1983 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት አጋማሽ በነበሩት ጊዜያትም፤ ጓድ የመቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ በትግራይ ራስ ገዝ አስተዳደር የኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ ሆኖም እያገለገለ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ዓለም የተለየው፤ ታኅሣሥ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ነበር፡፡ የቀብሩ ሥነ-ሥርዓትም የተፈፀመው በአዲስ አበባ ከተማ በሳሊተ-ምህረት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስቲያን ታኅሣሥ 19 ቀን በጣም ጥቂት ወዳጆቹና በአጋጣሚ ማረፉን የሰሙ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ነው፡፡ መቶ አለቃ ስለሺ የሁለት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
አዲስ ገሠሠ
አቶ አዲስ ገሠሠ ከአባታቸው ከግራዝማች ገሠሠ መንገሻ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አስናቀች መልሴ ጥር 8 ቀን 1945 ዓ.ም በቀድሞ ኢሊባቦር ጠቅላይ ግዛት ጎሬ ከተማ ተወለዱ፡፡ በቦብ ማርሌይ ቤተሰቦች የተዘጋጁትንና ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር ድረስ የተካሄዱትን ዓለም አቀፍ የሬጌ ሙዚቃ ኮንሰርቶች ሐሳብ ከመጠንሰስ ጀምሮ ለ22 ዓመታት ያህል በኃላፊነት መርተዋል፤ አስተዳድረዋልም፡፡ በዚሁ የአስተዳደር ዘመናቸው በዘረጉት መዋቅር የቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) የመጀመሪያ አልበም በማኔጅመንት በመምራት፣ እንዲሁም የእጅጋየሁ ሽባባውን (ጂጂን) ተወዳጅ አልበም ከአጋራቸው ፓልም ሪከርዲንግ ጋር በመሆን እንዲሠራ በማድረግ ረገድ የነበራቸው አስተዋፅኦ የጎላ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ጃኖ ባንድ››ን በመመሥረትና ለልጆቹ ውጤታማነት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ፤ እንዲሁም ‹‹ጃናናይት›› የተባለ ተሰጥኦ ያላቸውን ሴቶች ያቀፈ ባንድ በማቋቋም ያደረጉት ጥረት ሁልጊዜም የሚወሳ ነው፡፡መሠረት እስካሁን ድረስ በየዓመቱ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የሬጌ ሙዚቃ ፌስቲቫል በማይናወጥ መሠረት ላይ አፅንተዋል፡፡
የቦብ ማርሌይን 60ኛ ዓመት የልደት በዓል ለመዘከር የሚዘጋጀውን ‹‹አፍሪካ ዩናይት›› ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ዝግጅት ኢትዮጵያን መዳረሻ እንዲያደርግ አድርገዋል፡፡ አንድ ዓመት ሙሉ የፈጀ ታላቅ ዘመቻ በማካሄድም በ1997 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የተካሄደው ታሪካዊ የሙዚቃ ፌስቲቫል በታላቅ ስኬት እንዲጠናቀቅ አስችለዋል፡፡ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ሶስና ሽፈራው ጋር በነበራቸው የፀና ትዳርም አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡ አቶ አዲስ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ በአሜሪካ ኒውጄርሲ ግዛት ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል፡፡ የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸውም ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ኢንጂነር ካሳ ገብሬ
ኢንጂነር ካሳ ገብሬ በ1926 ዓ.ም በደብረ ታቦር ተወልደው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በምህንድስና ሙያ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ላይ ሀገራቸውን አገልግለዋል። ከነዚህም ውስጥ፦ በትምህርት ሚኒስቴር በዋና መሃንዲስነት፣ በከተማ ልማት ሚኒስትርነት፣ በሕንጻ ኮንስትራክሽን ሚኒስትርነት እንዲሁም በሌሎች በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነቶች አገልግለዋል። በሶማሊያ ወረራ ጦርነት ወቅት አገርን ከወራሪ ኃይል ለመታደግ 300 ሺህ ህዝባዊ ሠራዊት የሰለጠንበትን የታጠቅ ጦር ሜዳ ግንባታ በማይታመን ፍጥነት አሰርተዋል። በየጦር ግንባሩ ከሠራዊቱ ጋር እንደ ወታደር አብረው በመዝመት የሎጀስቲክስ ሥራዎችን በማስተባበር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። አየር ማረፊያዎችን፣ የወታደር ማሰልጠኛ ካምፖችን፣ ፋብሪካዎችንና ሌሎች ትልልቅ ተቋማትን በማስገንባት መርተዋል።
ኢንጂነር ካሳ ገብሬ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ከፈይ ወሌ ጋር ለ52 ዓመታት የዘለቀ የትዳር ህይወት የነበራቸው ሲሆን በዚህም ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶችን በጠቅላላው 4 ልጆችን አፍርተዋል። በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቶ ካሳ ገብሬ የቀብር ስነስርዓታቸው በአሜሪካን አገር ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል፣ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ/ም ተፈጽሟል፡፡
ብ/ጄ ውበቱ ፀጋዬ
ከአባታቸዉ አቶ ፀጋዬ ይመር እና ከእናታቸው ወይዘሮ እህልነሽ ገ/ሚካኤልም ሰኔ 12 ቀን 1933 ዓ.ም. ጐንደር ከተማ ተወለዱ፡፡ ከትዳር አጋራቸዉ ወ/ሮ ምንትዋብ ሰይፋ ጋር ነሐሴ 27 ቀን 1964 ዓ.ም. ተጋቡ፡፡ የሁለት ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡ በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ በጦራቸው ፊት በናቅፋ ግንባር ከኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም እጅ የጄነራልነት ማእረግ ያገኙ መኮንን እንደነበሩ የሚያስታውሶቸው አንዳንድ የቀድሞ ባልደረቦቻቸው፣ አንዳንዶችም የናቅፋው ጀግና ይሏቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ ለ32 ዓመታት ያገለገሉት ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ ፀጋዬ፣ “ሁሉም ነገር ወደ ሰሜኑ ጦር ግንባር” የሚል ከ700 ገፅ በላይ ያለው ታሪካዊና ሙያው ግምገማ ያጀበው መፅሀፍ ፅፈዋል፡፡
ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ በደርግ ዘመነ መንግሥት በኤርትራ ክፍለ ሀገር ተሰማርቶ የነበረውን የሁለተኛ አብዮታዊ ሰራዊት በአዛዥነት አገልግለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ደርግ ከመውደቁ በፊት በነበሩ ጥቂት ዓመታት በፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም ቢሮ በወታደራዊ አማካሪነት እና በብሔራዊ ውትድርና የሲቪል መከላከያ መምሪያ ኃላፊነትም መስራታቸው አይዘነጋም፡፡
በግንቦት 1981 ዓ. ም. ተሞክሮ በነበረው መፈንቅለ መንግስት ተሳትፎ ተጠርጥረው ለሁለት ዓመት በታላቁ ቤተ መንግስት የታሰሩት ብርጋዴየር ጄነራል ውበቱ፣ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ አስቀድሞ ከእስር ተለቅቀዋል። ብ/ጄ ውበቱ ከረጅሙ የስደት ዘመናቸው በኋላ ኑሯቸውን በአገር ውስጥ ቢያደርጉም አሜሪካን ሀገር ለህክምና ሄደው ነበር ህይወታቸው ያለፈው፡፡ በመስከረም የመጀመሪያው ሳምንት 2018 ዓ.ም፡፡ ብ/ጄኔራል ውበቱ ፀጋዬ በተሰደዱበት በአሜሪካ ሀገር በነበሩበት ወቅት በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የጀግናው የጦር መሪ አስክሬን ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ በነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሃውልት ምረቃና የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጽሞለታል፡፡
ፕሮፌሰር አመዘነ ታደሰ
ፕሮፌሰር አመዘነ ታደሰ ጥር 1 ቀን 1963 ዓም አዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። አባታቸው አቶ ታደሰ ሮበሌ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ (አሁን እማሆይ) እማሙ ገቢ ይባላሉ። ፕሮፌሰር አመዘነ በሰሩባቸው ተቋማት ውስጥ ህክምና ከመስጠት ጎን ለጎን በተለያዩ ደረጃዎች ሃገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ከነዚህም ውስጥ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀዶ ጥገና ክፍል ሃላፊ፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የህፃናት ቀዶ ጥገና ክፍል ሃላፊ፣ የSurgical Skills Lab ተባባሪ ዳይሬክተር፣ የSimulation Center of College of Social Sciences ተባባሪ ሊቀመንበር፣ በድህረ ምረቃ ትምህርት ክፍል የድህረ ምረቃ ኮሚቴ ሊቀመንበር፣ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት፣ የምስራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡባዊ አፍሪካ የህፃናት ቀዶ ጥገና ፕሮግራም Panel Head፣ እንዲሁም የአሜሪካ የቀዶ ህክምና ኮሌጅ አባል ነበሩ።
በመጨረሻም ፕሮፌሰር አመዘነ ታደሰ ከትምህርታቸው እና ስራቸው ባሻገር ባለው ህይወታቸውም ከዶ/ር ራሔል ደምሰው ጋር ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በትዳር በመጣመር ደስተኛ ህይወት ይመሩ የነበረ ሲሆን ከዚሁ ትዳራቸውም ሁለት ወንዶች ልጆች እና አንዲት ሴት ልጅ በድምሩ ሶስት ልጆችን አፍርተዋል። ባደረባቸው ህመም ምክንያት በአሜሪካን ሃገር እና በኢትዮጵያ ውስጥ በህክምና ሲረዱ ቢቆዩም የፈጣሪ ጥሪ ደርሷቸው በርካታ አገልግሎት ሊሰጡ በሚችሉበት ዕድሜ ላይ እያሉ ጥቅምት 5 ቀን 2018 ዓም ልክ ከረፋዱ 5 ሰዓት ከሩብ ላይ በተወለዱ በ54 ዓመት ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የፕሮፌሰር አመዘን ታደሰ አስክሬን ሽኝት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፡ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተካሂዷል፣ ሥርዓተ ቀብራቸውም ጥቅምት 7/2018 ዓ/ም በሀዋሳ ከተማ ተፈጽሟል፡፡
ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው (ሰሜ-ባላገሩ)
ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው (በቅጽል ስሙ “ሰሜ-ባላገሩ”) ከአባቱ ከአቶ በለው ሹምየ እና ከእናቱ ከወይዘሮ እናትነሽ ቢልልኝ መስከረም 17 ቀን 1960 ዓ.ም. ውብ በሆነችው፣ የአባይ እና የጣና መፍለቂያ በምትባለው ባህር ዳር ከተማ ተወለደ። ያደገውም በዚሁ ከተማ “ቀበሌ 03” (በተለምዶ አባ ፋሲሎ ትምህርት ቤት አካባቢ) በሚባለው ሰፈር ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ ለድምፅና ለሙዚቃ ልዩ ፍቅርና ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ የነበረው ሲሆን፣ በሰፈሩና በጓደኞቹ ዘንድ በማራኪ ድምፁ እና በደግነቱ እጅግ ይታወቅ ነበር። ሕዳር 11 ቀን 1978 ዓ.ም. በወጣትነት ዕድሜው የጎጃሙ ዝነኛ የኪነት ቡድን “ግሼ አባይ” አባል ለመሆን በቃ።
በ”ግሼ አባይ” ውስጥ በርካታ ምርጥ ባህላዊ ስራዎችን ያቀረበ ሲሆን በተለይም ከታዋቂዎቹ ድምፃውያን ከነይሁኔ በላይ እና ከሀብቱ ንጋቱ (አንሙቴ) ጋር በመሆን ያቀረበውና ለአራት አስርተ ዓመታት ያህል በሕዝብ ልቦና ውስጥ ታትሞ የኖረው “አንቱየዋ” የተሰኘው አስደናቂ ሙዚቃዊ ድራማ በታሪኩ ትልቅ ቦታ አለው። ሰማኸኝ በጥበብ ህይወቱ ስኬታማ እንደነበረው ሁሉ በቤተሰብ ህይወቱም የተባረከ አባት እና ባል ነበር። በ1982 ዓ.ም. ከወይዘሮ ገበያነሽ አባተ ጋር የትዳር ህይወት የመሰረተ ሲሆን የአራት ታላላቅ ምሁራን ወንድ ልጆች አባት ለመሆን በቅቷል፡፡ ሰሜ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመደበኛ በላይ የሆነ ውፍረቱ ይህ ነው የተባለ የጤና ችግር እንዳልፈጠረበት በመገናኛ ብዙሃን ተናግሮ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ውፍረቱን ለመቀነስ የተለያዩ የህክምና ዘዴዎችን ሲከታተል የቆየ ሲሆን ጥሩ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲገልጽ ነበር።
በመጨረሻም፤ ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጠዋት የድካም ስሜት ተሰምቶት በልጆቹ አማካኝነት ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ ሳለ በድንገት በመድከሙ፣ ሆስፒታል ደርሶም እርዳታ ቢደረግለትም ባለማገገሙ ብዙም ሳይቆይ በተወለደ በ58 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ህልፈቱ በኢትዮጵያ የሙዚቃ የትያትር እና የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ላይ ትልቅ ክፍተት የፈጠረ የሀዘን መርዶ ነው። ስርዓተ ቀብሩም ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በክብር ተፈፅሟል፡፡
ድምፃዊት ራሔል ዮሐንስ
በአዲስ አበባ ከተማ በካዛንቺስ አካባቢ መጋቢት 20 ቀን 1938 ዓ.ም. ከአባቷ አቶ ዮሐንሰ መኰንንና ከእናቷ ከወ/ሮ ወይንሸት ጎንፋ የተወለደችው የቀድሞዋ ድምፃዊት ራሔል ዮሐንሰ፣ “ሃና ሃና” በተሰኘው ዝነኛ ዘፈኑ ከሚታወሰው ታናሸ ወንድሟ ሰይፉ ዮሐንሰ ጋር በቄሰ ትምህርት ቤት እሰከ ዳዊት ድጋም ድረስ የተማረች ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአሰፋ ወሰን ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ በቀድሞው የኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት አጠናቃለች፡፡ በሙዚቃ ሕይወቷ ካከናወነቻቸው ሥራዎቿ መካከል በ1983 ዓ.ም. በአገር ባሕል ሙዚቃ ገናና ከነበሩት ከባህሩ ቀኜና ከይርጋ ዱባለ ጋር የተጫወተቻቸው ዘፈኖች ከአድማጮች ይሁንታን እሰገኝቶላታል። ሌሎቹ ሥራዎቿ አራዳ፣ ትዝታና አገሬ ኢትዮጵያ በተወዳጅነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከድምፃዊነቷ ባሻገር የዜማ ደራሲም ነበረች። ምኒልክ፣ አየር ኃይላችን፣ የአሰናቀች ወርቁን እንደ ኢየሩሳሌም በራሷ ዜማ ያደሰችበት ተጠቃሽ ሥራዎቿ ናቸው፡፡ የመጨረሻ ሥራዋ በያሬድ ተፈራ የተቀናበረው “ዘናበል” የተሰኘው አልበሟ ነበር። ከያኒት ራሔል ባደረባት ሕመም ምክንያት በሕክምና ስትረዳ ቆይታ በ80 ዓመቷ ሰኔ 28 ቀን 2018 ዓ.ም. አርፋ፣ ሥርዓተ ቀብሯ በማግሥቱ ሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ራሔል የሰድሰት ልጆች እናት፣ የ14 የልጅ ልጆች እያት፣ እንዲሁም የአምስት የልጅ ልጅ ልጆች ቅድመ አያት ነበረች፡፡
ታላቁ የእግር ኳስ ሰው ፍሰሐ ወልደአማኑኤል
አቶ ፍሰሐ ወልደ አማኑኤል፣ ከአባታቸው በጅሮንድ ወልደ አማኑኤል ደምሴ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አየለች በሻህ በሐረር ልዩ ስሙ “ደደር” በሚባል አካባቢ በሰኔ 1941 ዓ.ም ተወለዱ። ለቤተሰባቸውም 4ኛ ልጅ ናቸው፡፡ ፍስሃ ከ1957 – 59 በተከታታይ ሻምፒየን የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን አባልም ነበር፡፡ ፍሰሐ ወ/አማኑኤል፣ ሀገራቸውን በ4 የአፍሪካ ዋንጫ በመወከል የተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው በ6ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ 9 ቁጥር ለብሰው ያሳዩት ብቃት በኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ምንጊዜም የማይረሳ ነው፡፡
በ1961 ዓ.ም ባገኙት ነፃ የትምህርት ዕድል ምክንያት ወደ አሜሪካ ሀገር ያቀኑት ፍሰሐ ወ/አማኑኤል የካሊፎኒያ ሎስአንጀለስ ዩኒቨርሰቲ ተቀላቀሉ፡፡ በፖለቲካ ሳይንስም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ ፍስሃ በአሜሪካ አሁን ላይ በየአመቱ በታላቅ ድምቀት የሚካሄደውን የኢትዮጵያውያን አመታዊ የኳስ ውድድር በ1975 ከጀመሩ ሰዎች አንዱ ነው፡፡
ታዋቂውና አንጋፋው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታ አቶ ፍስሐ ወልደአማኑኤል (ኳስ ፊደሉ) ነሐሴ 2018 ዓ.ም (ኦገስት 2026) በተወለዱበትና በሚኖሩበት ሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፣ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሎስአንጀለስ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ጋሽ ፍስሃ በሚኖርበት በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ በማኅበረሰቡ የተከበረ፣ ከሁሉም ሰው ጋር መግባባት የሚችል፣ አገሩንና ህዝቡን የሚወድ፣ በጋብቻ ከ50 አመታት በላይ የኖረ የሁለት ሴት ልጆች አባት እና የአራት የልጅ ልጆች አያት ነበር፡፡
አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ
አምባሳደር ዶክተር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ከ50 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በታማኝነትና በደመቀ ሁኔታ ያገለገሉ አንጋፋና ቀዳሚ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ነበሩ፡፡ በሙያ አጋሮቻቸው ዘንድ ‹‹ተንቀሳቃሿ የአፍሪካ ጉዳዮች ኢንሳይክሎፒዲያ›› በሚል የቅጽል ስም የሚታወቁት አምባሳደር ቆንጂት፣ በታሪክ ከዮዲት እምሩ በመቀጠል የኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደር በመሆን በርካታ ሴቶች ወደ ዲፕሎማሲው ዓለም እንዲቀላቀሉ በር የከፈቱ የሴቶች አርዓያ ናቸው፡፡
አምባሳደር ቆንጂት ውልደታቸው በ1932 ዓ.ም አካባቢ በሐረር ከተማ ቢሆንም፣ ያደጉት ግን በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ የነበሩት ቆንጂት፣ በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (University College London) በዓለም አቀፍ ግንኙነት (International Relations) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1954 እ.ኤ.አ. አግኝተዋል፡፡ በ1963 በኒውዮርክ በሚገኘው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የካርኒጊ ፌሎውሺፕ (Carnegie Fellowship) ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
እኚህ የዲፕሎማሲ ቁንጮና የአገር ባለውለታ፣ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ86 ዓመታቸው መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መሪዎች ለአምባሳደሯ ጥልቅ ሐዘናቸውንና ታላቅ አክብሮታቸውን ገልጸዋል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም 2019 ዓ.ም
