ታዋቂው የኒውዮርክ የጉዞ መጽሔት “Travel + Leisure” ህንድን የ2027 የዓመቱ ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ አድርጎ መምረጡ ተገለጸ። ዕውቅናው የሀገሪቱን ባህላዊ ብዝኃነት፣ የተፈጥሮ ውበትና የቱሪዝም መስህቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ እንዲታወቁ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
ህንድ ከኡዳይፑር የንጉሣዊ ቅርሶችና ከሙምባይ ደማቅ የከተማ ሕይወት እስከ ሂማሊያ ተራሮችና የላክሻድዊፕ ደሴቶች ያሉ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦች ያሏት ሀገር ናት።
መጽሔቱ የሀገሪቱን የበለጸገ ባህል፣ የምግብ ዓይነቶች፣ ባህላዊ ወጎችና የሕዝቧን አቀባበል ለዕውቅናው ከተጠቀሱ መስህቦች መካከል አካትቷል።
የህንድ ቱሪዝም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን እየሳበ ባለበት ወቅት፣ ይህ ዕውቅና የቱሪዝም ዘርፉን የበለጠ ለማነቃቃት፣ የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግና ሀገሪቱን በዓለም የጉዞ ገበያ ይበልጥ ተወዳጅ ለማድረግ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።
