በደረጀ ይመር
ማስፈንጠሪያ
ግዮን መጽሔት :- የአብርሆት ዘመን ፍሬ የሆነው የፈረንሳይ አብዮት ለሰው ዘር አኑሮት ያለፈው አበርክቶ በቁጥር አይገፋም፡፡ በተለይ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ ካስማ የሚቆጠሩትን፤ በግብር ለየቅል፣ በኅላዌ ግን የማይነጣጠሉትን ወንድማማችነት፣ እኩልነት እና ነጻነትን ለአውደ ርዕይ በማቅረቡ ምክንያት በፋናወጊነት ይጠቀሳል፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ ብሶት የወለደው ሕዝባዊ አብዮት፤ የዘመናዊው ሥነመንግሥት የሚመራበት ሕገመንግሥታዊ ሰነድን በማስተዋወቅ ረገድ የጉልላት ሥፍራን ይይዛል፡፡ ከፈረንሳይ አብዮት ለጥቆ የመጣው ሕገመንግሥት በዋንኛነት ጣምራ ግቦችን ከግምት ጥፎ ነው ገቢራዊ የሆነው፡፡ ቀዳሚው ግቡ፤ በሃገረመንግሥቱ የሥልጣን መንበር ላይ የሚቆናጠጠው መንግሥት ሥልጣን እንዲገደብ አስተማማኝ ልጓም ማበጀት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች የሚከበርበት ሥርዓት እንዲፈጠር አስተማማኝ መደላድል ማኖር ነው፡፡
የሕዝብ ሉኣላዊነት መገለጫ የሆነው ሰነድ ከሀገራችን ሥርዓተመንግሥት ጋር የተዋወቀው በንጉሡ ዘመነ መንግሥት በ1923 ዓ.ም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሀገራችን የሥርዓተመንግሥት የታሪክ ሒደት ውስጥ የአሁኑን የሕወሓት/ኢሕአዴግን ጨምሮ አራት ሕገመንግሥታዊ ሰነዶች ተቀርጸው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡
ለዛሬ የመጽሐፍ ዳሰሳ ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ፤ የ1997 ዓ.ም ድህረ ምርጫ ሁከት አጣሪ ኮሚሽን ሰብሳቢ የነበሩት ዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል ለሕትመት ብርሃን ያበቁት ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ ሽንጣም ድርሳን፣ ‹‹ሕገመንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› በሚል ርዕስ፣ በ297 ገጽ የቀነበበ እና በሠላሳ ሁለት ምዕራፎች የተከፋፈለ ጠንከር ያለ ሒስ የታጨቀበት ነው፡፡ በርግጥ፤ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ለሕትመት ብርሃን ከበቁት መጻሕፍት መካከል የነገደ ጎበዜ ኩርማን ድርሳን ትርጉም ሰጥታኛለች፡፡ ይቺ በመዳፍ ልክ የተከረከመች ድርሳን ለአንባቢያን በብዛት እንድትዳረስ ምክንያት የሆነው በረከት ስምኦን በምርጫ 97 የቴሌቪዥን ክርክር ላይ በክፉ ማብጠልጠላቸው ነበር፡፡ ‹‹የማስታወቂያ ፉንጋ የለውም›› እንዲሉ፤ በወቅቱ ጸሐፊው ነገደ ጎበዜ፣ ‹‹የበረከት ውለታን ከፍዬ አልጨረሰውም ፤ በቴሌቭዥን ላይ ያለምንም ክፍያ መጽሐፌን ባያስተዋውቁልኝ ኖሮ፤ በርካታ አንባቢያን ዘንድ አይደርስም ነበር›› ብለዋል፡፡ ከነገደ ጎበዜ መጽሐፍ በኋላ ለእኔ በአቀራረቡም ሆነ ባነሳቸው ቋጥኝ ቁምነገሮች፣ የዳኛ ፍሬሕይወት ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› ድርሳን በብዙ ረገድ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
ሁለቱ የገሃነም ጫፎች
ጸሐፊው በሕገመንግሥታዊው ሰነድ ዙሪያ የሚራመዱትን ማዶ ለማዶ የሆኑ የተቃርኖ አቋሞችን ለአውደ ርዕይ በማቀረብ ነው ኂሱን የሚያሟሸው፡፡ ‹‹ሕገመንግሥቱ ተቀዶ ካልተጣለ ለሀገራዊ ምስቅልቅሉ ምንም ዓይነት መላ ማበጀት አይቻልም›› የሚል ሥርነቀላዊ አቋም በአንደኛው ጠርዝ የሚያስተጋቡ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ፡፡ በአንጻሩ ከሕወሓት ጋር ኩታገጠም የፖለቲካ እሳቤን የሚያቀነቅኑ ልሂቃን እና ቡድኖች ደግሞ፤ ‹‹ሕገመንግሥቱ የሚለወጠው በመቀብራችን ላይ ነው›› ይላሉ፡፡ የሁለቱም አቋም አንዱን በአንዱ የሚያጣፋ ነው፡፡ በአንዱ መቃብር ላይ ሌላው አበባ ያኖራል፡፡ ንጽጽራዊውን ዕይታ፣ የሩቅ ምሥራቅ ፋላስፎች ‹‹በሁለት ገሀነም መካከል ገነት አለ›› በሚል ግሩም ምልከታ ይገልጹታል፡፡ ጠርዝ እና ጠርዝ ላይ የተሰየሙት አቋሞች የገሃነሙ ጫፍ ናቸው፡፡ አማካኙ፣ ገነቱ ከአመክንዮ ያልተራቆተ፣ በሰከነ ውይይት ቋጠሮዎች የሚፈቱበት አውድ ነው፡፡ ጸሐፊው ይህንን ምራቅ የሚያስውጥ ግብዣ እንካችሁ ብሎ ነው፣ ወደ ውስጥ የሚያንደረድረን፡፡
የሰነዱ ዘረመል እንዴት ተበጃጀ?
በ1960ዎች የተማሪዎች ንቅናቄ እንደዋዛ በጥራዝ ነጠቅነት የተዘራው የግራ ዘመም ፖለቲካ ዛሬ ለገባንበት ቅርቃር መነሾ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡ ‹‹Modernity, Eurocentrism, and radical politics in Ethiopia, 1961-1991›› በሚለው ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ “instead of Marxism adapting to Ethiopia, it was made to adapt to Marxism” በሚል ግሩም ሐረግ ገልጾታል፡፡”ማርክሲዝምን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ከማስማማት ይልቅ ፤ ኢትዮጵያ ናት ለማርክሲዝም ነባራዊ ሁኔታ እንድትመች የተከረከመችው፡፡” እንደማለት ነው፡፡
በአልባኒያው የሄቨር ሆንጃ አክራሪ የሶሻሊዝም እሳቤ ተጠምቆ ሥልጣን ላይ የወጣው የ‹‹ያ ትውልድ›› ፍሬ ሕወሓት/ኢሕአዴግ፤ በተንሸዋረረው ርዕዮተዓለማዊ አረዳድ ምን ያህል እንደቆረበ አንዱ ማሳያ፣ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች›› ለተባለ እንግዳ ማንነት ያለው ታማኝነት እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ይህ ምንነቱ በቅጡ ያልተብራራ ግራ እሳቤ የ1987ቱ ሕገመንግሥት የማዕዘን ድንጋይ እንዲሆን መደረጉ ውሎ አድሮ ፖለቲካው ሐዲዱን እንዲስት ትልቁን ድርሻ ተጫውቷል፡፡ ጸሐፊው የምስቅልቅሉ ዘፍጥረት የሚጀምረው ፓርቲው ከትግል እንስቶ የቆረበበትን የግራ ዘመም ርዕዮተዓለም ለመተው ባለመፈለጉ የተነሳ ነው ሲል ይሞግታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋቢ ያደረገው ፓርቲው ለጽንሰሐሳቡ ያሳየውን አምልኮ ነው፡፡ ገጽ 11 ላይ ከሰፈረው በጥቂቱ፡-
በማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ውስጥ የግለሰብ እና የኅብረተሰብ ልዩነትና አንድነት “የግለሰቡ ጥቅም ሊረካ የሚችለው በወል ጥቅም ማደግ፣ የወል ጥቅም ማደግ የሚችለው በግለሰቡ ንቁ ተሳትፎ ነው” በሚል ተገልጾ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች የብሔሮች ብሔረሰቦች ሕዝቦች የወል መብትና ጥቅም ሲጠበቅ የግል ጥቅም ይጠበቃል የሚለውን ኮሚኒስታዊ ጽንፈኛ እሳቤ መዋቅራዊ እንዲሆን የማዕዘን ድንጋይ ጥለዋል፡፡
የሕገመንግሥቱ አልፋ እና ኦሜጋ የሆነው ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች›› የተባለው የወል ማንነት የተቀዳው ከትናንቱ ቆሞ ቀር የግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ ከጸሓፊው ትንታኔ እንረዳለን፡፡
ሕገመንግሥቱ ገና በመንደርደሪያው ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ከሉአላዊ ሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው ቆርሰው ኢትዮጵያን እንደፈጠሯት ደንግጓል፡፡ በሰነዱ መሠረት፤ ኢትዮጵያ ትናንት በ1987 ዓ.ም በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መልካም ፍቃድ ምክንያት የተፈጠረች ልጅ ናት፡፡ ለዚህም ነው ሕገመንግሥቱ ‹‹ከፌደራል ሥርዓት ይልቅ የኮፌንደራል ሥርዓትን ያወለደ ነው›› ተብሎ የሚሞገተው፡፡ እነዚህ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአንቀጽ 8 መሠረት የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤት ሆነዋል፡፡ ለሉኣላዊ ሥልጣናቸው መገለጫ ደግሞ በአንቀጽ 47 መሠረት የራሳቸው ቤት (ክልል) ተሰጥቷቸዋል ፤ ይህም ካልተስማማቸው በአንቀጽ 39 አማካኝነት የራሳቸውን ‹‹ባናና ሪፐብሊክ›› እንዲመሠረቱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ በዚህ ሐዲት ውስጥ በዜግነት ወይም በግለሰብ የሚገኘው ማንነት ሜዳ ላይ ተጥሏል፡፡ ጸሐፊው የሚጎፈንነው እውነታ ተለንቅጦ የተበጃጀበትን ዘረመል፣ ሽክን ባለቋንቋ ንቃታችንን ለማብራት እያሰለሰ ደፋ ቀና ይላል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ሥልጣን መያዣ ዋንኛ ቅኝት ብሔር/ብሔረሰብ ላይ ሲቸነከር የሚያመጣውን ጣጣ በምዕራፍ 31 በግሩም ሁኔታ አመላክቷል፡፡
አልቦ የቁጥጥር እና ሚዛን ሥርዓት
ጸሐፊው ሕገመንግሥቱ ለቁጥጥር እና ሚዛን ሥርዓት/Checks and balance/ ምን ያህል ባዕድ እንደሆነ ለመሞገት በዋቢነት የሚያነሳው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚናን ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚወልደው ሕገመንግሥታዊ ሰነድ፣ የሦስቱ ምክር ቤቶች ቁመናን ልክ እንደ ማበጠሪያ ጥርስ በእኩል ደረጃ እንዲከረከሙ ያደርጋል፡፡ ግንኙነታቸው አንዱን ሌላውን ለማስገበር በሚመች መልኩ፣ በተዋረዳዊ ሰንሰለት የተዋቀረ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ፤ የአንዱ ምክር ቤት ከሌላው እንዳይበልጥ በአግድሞሽ የቁጥጥር እና ሚዛን ሥርዓት ልጓም እንዲበጅለት ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት በእኛ ሀገር ዱካውም የለም፡፡ በተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት መካከል ያለውን ግንኙነት መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ በመካከላቸው የሥራ ክፍፍል እንጂ፣ የሥልጣን ከፍፍል የለም፡፡ መጽሐፉ የአልቦ የቁጥጥር እና ሚዛን ሥርዓቱን ስስ ጎን ከምክር ቤቶቹ ሚና አንጻር ይኄሳል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሌሎች የፌደራላዊ ሥርዓት በሚከተሉ ሀገራት ዘንድ ያለው ቁመና እና ሚና ክእኛ ጋር ለየቅል ነው፡፡ ም/ቤቱ በሕገመንግሥቱ መሠረት የተዋቀረበት መርህ፣ ፀረ ፌዴራላዊ መንገድን ተከትሎ ነው፡፡ በፌደራል ሥርዓት ውስጥ እንደ ፌዴሬሽን ያሉ የግዛት ተወካዮች የሚካተቱበት ምክር ቤት፣ ዋንኛ ዓላማ ከተወካዮች ምክር ቤት ጋር መሳ ለመሳ ሆኖ ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንዲኖረው ነው፡፡ ለአብነት፤ የአሜሪካውን የፌዴሬሽን ም/ቤትን /ሴኔትን/ ብንወስድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት/ኮንግረስ/ ጋር እኩል ሕግ የማውጣት ሥልጣን አለው፡፡ ሁለቱ ምክር ቤቶች (ሴኔት እና ኮንግረስ) ከ2/3 ድምጽ በላይ አጽድቀው ያሳለፉትን ረቂቅ፣ የአስፈጻሚው ቁንጮ የሆነው ፕሬዝዳንቱ የመሻር ሥልጣኑን/ቬቶ ፓወርን/ ተጠቅሞ ውሳኔውን ማጠፍ አይችልም፡፡
በአንጻሩ የእኛ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከሕግ አውጪነት ሚና ተገልሎ ወይም የበይ ተመልካች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምክር ቤቱ፣ ሕገመንግሥቱ የሰጠው ሥልጣን፣ የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን ጉዳዮችን እና አሻሚ የሕገመንግሥት ትርጓሜ ላይ ብይን መስጠት እንዲችል ነው፡፡ ክልሎች ከድንበሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በራሳቸው እልባት መስጠት ከተሳናቸው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ብይን እንደሚሰጥ አንቀጽ 48 ላይ ተደንግጓል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ያልሆነ የካድሬዎች ስብስብ፣ ሕገመንግሥቱን በተመለከተ ሚዛናዊ ፍርድ ይሰጣል ብሎ ማሰብ የዋህንነት ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የጸሐፊውን ሙግት በገጽ 126 ላይ እናገኛለን፡-
ሕገ መንግሥቱን የመጣስ ችግር በባሕሪው የሚመነጨው በዋናነት ከመንግሥት ነው ካልን ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል? ወይንስ አልተጣሰም? የሚለውን ክርክር የመዳኘት ሥልጣን መልሰን የመንግሥት አካል የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲመረምረው ማድረግ የመንግሥት ራሱ ሕግ ከጣሰ በኋላ ራሱን መልሶ በራሱ እንዲዳኘው መፍቀድ ስለሆነ አንድ አካል በራሱ ጉዳይ ራሱ ዳኛ ሊሆን አይችልም የሚለውን መሠረታዊ የሕግ መርህ ይጥሳል የሚል ክርክር ያስነሳል፡፡
በሌሎች ሀገሮች ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ለሆነ የዳኝነት አካል ነው የሚሰጠው፡፡ ጸሐፊው ሕገመንግሥት የመተርጎሙም ጉዳይ ለመደበኛ ፍርድ ቤት ወይም ሰነዱን ለመተርጎም ብቻ ተብሎ ለተቋቋመ የሕግ አካል ብቻ የሚሰጥበትን ፍኖተ ካርታ በምዕራፍ 18 ላይ አመላክቷል፡፡
መጽሐፉ የሳሳባቸው ጎኖች
ጸሐፊው ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተያይዞ የሀገራችን የፖለቲካ ምሕዳር ላይ የጉልላት ሥፍራን ለያዘው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት የሰጠው ሽፋን በቂ አይደለም፡፡ ትርክቱ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በሕገመንግሥቱ መንደርደሪያ ላይ እንደዋዛ ሻጥ ያለው ‹‹የተዛባ ግኑኝነትን ለማረቅ›› የሚለው ሐረግ ውሎ አድሮ ትልቅ የፖለቲካ ሽንቁር ፈጥሯል፡፡ ጨቋኝ ተጨቋኝ ‹‹ዳይኮቶሚ›› የዚህ ስንኩል ሐረግ የአብራክ ውጤት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
‹‹ጨቋኝ›› እና ‹‹ተጨቋኝ›› የሚለው ዳይኮቶሚ ምንጩ የተንሸዋረረ ሶሻሊስታዊ ግንዛቤ ነው፡፡ በሶሻሊስታዊ ትንትኔ ኅብረተሰባዊ ዕድገት የሚተነተነው በመደባዊ ቅራኔ ሲሆን መደባዊ ቅራኔው በአንብሮ(thesis) እና በተቃርኖ(antithesis) መስተጋብር አስተጻማሮን(synthesis) ይፈጥራል፡፡ ለአብነት በካፒታሊዝም ሥርዓት ውስጥ ላብአደሩ እና ከበርቴው ተቃርነው በአስተጻምሮ መልኩ ሶሻሊዝምን ይወልዳሉ፡፡ ይህንን ዲያሌክቲካዊ ጭውውት በሀገራችን ነበራዊ ሁኔታ ዱካውን አናገኘውም፡፡ ያ ትውልድ ውጥምዱን ያለፈው ተቃርኖውን ለብሔረሰባዊ ማንነት በመስጠት ነበር፡፡ የ ያ ትውልድ የአብራክ ውጤት የሆነው ሕወሓት በበርሃ በቀረጸው ማኒፌስቶ ላይ በግልጽ ሰፍሮ የምናገኘው ‹‹ጨቋኙ የአማራ ገዢ መደብ›› ምንጩ የትናንቱ የተንሻንፈፈ የዋለልኛዊ ንጽረተ ዓለም ውጤት ነው፡፡
የሕወሓት ማኒፌስቶ ግልባጭ ደግሞ በሕገመንግሥቱ መንደርደሪያ ላይ እናገኘዋለን፡፡ በጨቋኝ እና ተጨቋኝ የተዛባ ግንኙነት ማዶ ለማዶ የተሰየሙት ሕዝቦች በጋራ መጥተው የፈጠሩት ሰነድ ውሎ አድሮ ማኅብራዊ መስተጋብርን የሚበጣጥስ ሥርዓተመንግሥትን ወልዷል፡፡ በተለይ ላለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት በጨቋኝነት የተፈረጀው የአማራ ሕዝብ በሌሎች ብሔረሰቦች ዘንድ ጥርስ ተነክሶበት የመከራን ጽዋ ሲቀበል ኖሯል፡፡ ‹‹ዋለልኝ አልሞተም፣ ሕያው ነው›› የሚባለው አማራን በጨቋኝነት፣ ሌሎችን ብሔሮች ደግሞ በተጨቋኝነት የፈረጀ ሥርዓተመንግሥት ሥጋ ለብሶ በመመልከታችን ነው፡፡ ጸሐፊው የጨቋኝ ተጨቋኝ ዳይኮቶሚን የራሱ ምዕራፍ አብጅቶለት በተብራራ መልኩ ሊያሳየን ይገባ ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፍሬው በሚመዘንበት ጊዜ ይህን ስሁት ተቃርኖ በቅጡ አለመፈተሸ ሙግቱን ምሉዕ አያደርገውም፡፡
ጸሐፊው ብልጽግናን የብሔር ዘመም ድርጅት እንዳልሆነ ያሳየው ዳርዳርታ ለሂስ የሚያጋልጠው ነው፡፡ በገጽ 238 ላይ በብሔር ብሔረሰብ ተደራጅቶ ሥልጣን መያዝ የሚያመጣውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጣጣ ያመላከተ ሲሆን የመውጫ መፍትሔው ልክ እንደ ብልጽግና ሕብረብሔራዊ የሆነ ቁመናን ተላብሶ መደራጀት እንደሆነ ያስረግጣል፡፡ እዚህ ጋር የተቀመጠው የጸሐፊው ሐሳብ ግን ውሃ አያነሳም፡፡ ብልጽግና የሚመራው መንግሥት፣ ብሔር ተኮር ከሆነው የፖለቲካ አደረጃጀት አዙሪት ለመውጣት አሳማኝ አዝማሚያ እያሳየን አይደለም፡፡ እንደውም፤ በአንዳንድ ዘርፎች ከሕወሓት/ኢህአዴግ በባሰ መልኩ የእሳቤው ቁራኞ ሆኖ እንመለከታዋለን፡፡ ለአብነት፤ በቅርቡ የብቃት እና አቅም (meritocracy) ነጻ ቀጠና በሆነው ቢሮክራሲዊ አደረጃጀት ላይ የብሔር ቀመር በማበጀት ቆፈን ውስጥ የሚከት እርምጃዎችን ለአውደ ርዕይ አቀርቦልናል፡፡ ስለዚህ ብልጽግናን በነቢብ ‹‹ሕብረብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ነው›› ብሎ ከመፈረጅ ባለፈ ከብሔር/ብሔረሰብ የፖለቲካ አደረጃጀት ነጻ እንደወጣ ማሳያ ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባትም ጸሐፊው የብልጽግና ተሞክሮ ማንሳቱ ካልቀረ ሕጸጹን አብሮ ማመላከት ቢችል ኖሮ ትርጉም ይሰጥ ነበር፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ሕገመንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› መጽሐፍ ያነሳቸው የሙግት ሐሳቦች እና የመፍትሔ አማራጮች ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት (እዚህ ጋር የምክክር ኮሚሽንን ልብ ይሏል) ከምር የሚወስዳቸው ከሆነ ላለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት ሃገረመንግሥቱን በብርቱ ይንጡት ከነበሩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሽ ለመውጣት የሚቻልበትን ፈር ያገኛል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 234 2018 ዓ.ም
