ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አንጋፋው ድምጻዊ ግርማ ነጋሽ ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ:: ስርዓተ ቀብሩ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆች ፣ የሙያ አጋሮቹ እና አድናቂዎች በተገኙበት መስከረም 14/2019 በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
ከሙዚቃ ባለፈ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥ እንደ ስፖርት ጋዜጠኛ በመሥራት የበርካታ ዓመታት አገልጋይም ነበረ። አንጋፋው አርቲስት እና ጋዜጠኛ ግርማ ነጋሽ በ83 ዓመቱ ዕሮብ መስከረም 13- 2019 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የቀብር ሥነ-ሥርዓቱም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
በኢትዮጵያ ወርቃማው የሙዚቃ ዘመን በርካታ ተወዳጅ ሥራዎችን ያበረከተው አንጋፋው ድምፃዊና ጋዜጠኛ ግርማ ነጋሽ፣ ከእናቱ ከወይዘሮ አፀደ ውቤ እና ከአባቱ አቶ ነጋሽ ወ/ሥላሴ በ1936 ዓ.ም. አራት ኪሎ ፊት በር አካባቢ ተወለደ።
ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስም በሽመልስ ሀብቴና በኮከበ ጽባሕ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። በልጅነቱ የሙዚቃ ፍቅር ያደረበት ግርማ ነጋሽ፣ የሙዚቃ ሥራውን የጀመረው በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ባንድ ውስጥ ነበር።
በኋላም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር፣ በአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር፣ በድምፃዊነት ተቀጥሮ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ማሳረፍ የቻለ ታዋቂ ድምፃዊ ሆነ።
በሕይወት ዘመኑ ከተጫወታቸውና በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ከሆኑት የሙዚቃ ሥራዎቹ መካከል «ምነው ተለየሽኝ»፣ «የኔ ሐሳብ»፣ «አልበቃኝም ገና»፣ «እንገናኛለን»፣ «ቀለሜዋ»፣ «የኔ ውብ አይናማ» እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
ከ60 ዓመታት በላይ ዕድሜን የተሻገሩት እነዚህ የሙዚቃ ሥራዎች ታሪክና ትዝታን ተሸክመው አሁንም በሙዚቃ አድማጮች ዘንድ ተወዳጅነታቸውን ጠብቀው ይደመጣሉ።
ድምፃዊው ግርማ ነጋሽ ከዘፋኝነቱ ባሻገር በቀድሞው አጠራር ኮካ ኮላ ፋብሪካ የሽያጭ ባለሙያ ሆኖ አገልግሏል።
በ1959 ዓ.ም. በማስታወቂያ ሚኒስቴር በመቀጠርም በተለያዩ ክፍሎች፣ በተለይም በሥነ-ጽሑፍ ምርመራ (ሳንሱር) ክፍልና በመዝገብ ቤት፣ በሠራተኝነት ተሰማርቶ ሠርቷል።
በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በሹፌርነት፣ በኋላም በጋዜጠኝነት አገልግሏል።
ከደምሴ ዳምጤና ይንበርበሩ ምትኬ ጋር በመሆን የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅሙ ስፖርታዊ ትንታኔዎችንና ዜናዎችን በማዘጋጀት በጋዜጠኝነት አገልግሏል።
ድምፃዊና ጋዜጠኛ ግርማ ነጋሽ በቀደመው ዘመን በራስ ሆቴልና በግዮን ሆቴል የምሽት ክበቦች ውስጥ በሙያው ያዜመ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ውጭም በተለያዩ ሀገራት ሥራዎቹን ለማቅረብ የቻለ ስመ ጥር አርቲስት ነበር።
ድምፃዊና ጋዜጠኛ ግርማ ነጋሽ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ላበረከተው የማይተካ ሚና በሰሜን አሜሪካ የሙዚቀኞች ማኅበር አማካይነት የሕይወት ዘመን የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት በ2017 ዓ.ም. ተበርክቶለታል።
ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የሆነው ግርማ ነጋሽ፣ በተወለደ በ84 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አንጋፋው ድምፃዊ ግርማ ነጋሽ ባለትዳርና የሦስት ወንዶችና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር።
6 የልጅ፣ ልጅ አይተዋል።
ለቤተሰቦቹ፣ ለሙያ ባልደረቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለሚወዱት አድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን።
