የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአስርተ አመታት በላይ ሲጠቀምበት የኖረውን የንግድ ምልክት (Logo) በአዲስ የንግድ ምልክት ለመቀየር 600 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ ሲሰራ ነበር:: በዚህም መሰረት ባንኩ አዲሱን የንግድ ምልክት ይፋ የማድረጊያ ሰዓት ላይ ዕቅዱን ሰርዟል::
ምክንያቱ ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲሱ ሎጎ የፈጠራ እና የኢትዮጵያዊነት ገጽታ ጎድሎታል በሚል ባቀረቡት ትችት እንደሆነ ዛሬ ሪፖርተርስ ዘግቧል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ ለፕሮጀክቱ የተመደበው በጀት ብዙዎችን ሲያነጋግር ውሏል:: እኔ ግን እንደ ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ ባለሙያ ከገንዘቡ መነጋገሪያነት ባሻገር በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ የግሌን ምልከታ እና ጥያቄ ማስፈር ፈለግኩ::
በመጀመርያ ደረጃ የንግድ ምልክት (Logo) ምንድነው? ሎጎ ማለት የድርጅትን ብራንድ ማንነት (Brand Identity) ፣ እሴት (Values) እና ራዕይ (Vision) በአንድ ምስል ወይም ምልክት የሚያጠቃልል የምስል መታወቂያ (Visual Identity) ነው።
በቀላል አገላለጽ ሎጎ የአንድ ድርጅት ምርት ወይም አገልግሎት መለያ የሆነ ምልክት ነው። እንደ ሰው ስም ሎጎም አንድ ድርጅቱ በሌሎች ድርጅቶች ወይም ምርቶች መካከል በቀላሉ እንዲታወቅ ያደርገዋል።
ከዚህም ባሻገር ሎጎ የአንድ ድርጅት እና ደንበኛን ስነ-ልቦና የሚያስተሳስር፣ በማስተሳሰር በደንበኞች አዕምሮ ውስጥ የሚገነባ ስሜት ነው::
ይሄም በጊዜ ሂደት በደንበኞች ዘንድ እምነት እና ታማኝነት (Trust and Loyalty) ይገነባል። ደንበኞች አንድ ሎጎን ሲያዩ ከምስሉ ባለፈ የተለያዩ ስሜቶችን ፣ ትውስታዎችን እና ልምዶችን ያስታውሳሉ::
ለምሳሌ “Just Do It” የሚል ቃልን ድንገት ብንመለከት ወደ አዕምሯችን ጓዳ በፍጥነት ብቅ የሚለው Nike ጫማ ነው:: እንዲሁ ደግሞ የተጎመጠ የአፕል ፍሬ ምስል ብናይ ወደ አዕምሯችን በፍጥንት ብቅ ሊል የሚችለውን ብራንድ እና ምርትም ግልፅ ነው::
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (CBE) ለረዥም ጊዜ ሲጠቀምበት የኖረው ሎጎ ከህዝቡ ጋር ጥልቅ የስነ-ልቦና ትስስር የፈጠረ የብራንድ ካፒታል (Brand Equity) መገንባቱ የማይካድ ሃቅ ነው። ይህ ሎጎ ባንኩን ለሚያውቁት ሁሉ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ምልክት ሆኖ አገልግሏል።
እንደየደንበኛው ማንነት ሁሉም የራሱ የሆነ የስነ-ልቦና ትስስር ይኖረዋል:: (ቁጠባ ፣ የሲስተም ችግር ፣ መጉላላት ፣ የደህንነት ስሜት ፣ ሽልማት ፣ ወለድ ፣ ዕዳ ፣ ቦታ ጠቋሚነት ወዘተ) እነዚህ በሙሉ ባንኩ ከደንበኞቹ ጋር በሎጎው የሚፈጥረው ስነ-ልቦና ትስስር ናቸው:: ታዲያ ንግድ ባንክ አሁን ይሄን ሎጎ ለምን ሊቀይረው ፈለገ?
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ ድርጅት ሎጎውን ለመቀየር ወይም Rebrand ለማድረግ እጅግ አሳማኝ ምክንያት ሊኖረው ይገባል ብለው ይስማማሉ:: ለምሳሌ ወደ አዲስ የገበያ ዘርፍ የሚገባ ከሆነ:: የንግድ አቅጣጫ የሚቀይር ከሆነ::
ያለበትን አሉታዊ ምስል ለመቀየር ከፈለገ ወዘተ ብለው ያስቀምጣሉ:: ታዲያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሎጎውን ሊቀይር የፈለገው ከእነዚህ አሳማኝ ምክንያቶች በአንዱ ምክንያት ነው? ወይስ በኢ-ምክንያታዊ በፋሽን እና በውድድር መንፈስ ብቻ? ባንኩ የዘመናዊነት ገጽታን ለማላበስ ቢፈልግም ደንበኞቹ የለመዱትን ማንነት ችላ ማለቱ ትክክል ነው ወይ?
ንግድ ባንክ ድንገተኛ የሎጎ ለውጥ ማድረጉ ወደፊት የሚያመጣበት አሉታዊ ተፅዕኖዎችም አሉት:: ይኼም የደንበኞችን የረጅም ጊዜ የስነ-ልቦና ትስስር ማፍረስ ነው። ይህን ነገር ከዚህ በፊት የሞከሩ ድርጅቶችም ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል። ለአብነት ያህል:-
ታዋቂው የልብስ ድርጅት Gap ቀድሞ ሲጠቀምበት የነበረውን ሎጎ በድንገት በመቀየሩ ደንበኞቹ በንዴት ዘመቻ ከፍተውበት በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ ቀድሞው ሎጎ እንዲመለስ አስገድደውታል።
ሌላው የብርቱካን ጭማቂ አምራች ድርጅት የሆነው Tropicana ነው:: ትሮፒካና በ2009 ሎጎውንና ማሸጊያውን ሲቀይር ሽያጩ በ20% በመውረዱ በወር ውስጥ ወደ ነበረበት ተመልሷል።
እነዚህ ምሳሌዎች የሚያሳዩት ሎጎ የድርጅቱን ማንነት ብቻ ሳይሆን የደንበኞችንም ስሜት የሚወክል መሆኑን ነው። የንግድ ባንክ ሎጎውን በመቀየሩ ከላይ ከተጠቀሱት አሉታዊ ተፅዕኖዎች በተጨማሪ በህዝቡ ዘንድ የተገነባውን Emotional Attachment ሊያሳጣው ይችላል::
በብራንድ ማኔጅመንት ዘርፍ ታዋቂው ምሁር ማርቲ ኒውማየር (Marty Neumeier) “Your brand isn’t what you say it is. It’s what they say it is.” ይላሉ። “የእርስዎ ብራንድ እርስዎ የሚሉት አይደለም። ብራንድዎ ህዝቡ የሚለው ነው” የሚል ነው።
ይህ ንግግር የሎጎን ወሳኝነትና ከደንበኞች ጋር ያለውን ትስስር ያጎላል። ሎጎን በገንዘብ ብዛት መቀየር የሚሞከር ከሆነ የብራንድ ማንነት ሊሸረሸር እንደሚችል ይናገራሉ።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሎጎ ለመቀየር ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ማውጣቱ ስትራቴጂያዊ ውሳኔ ቢሆን እንኳ የህዝብን ስሜት እና የረጅም ጊዜ ታሪክን ካለማገናዘብ አንፃር ትክክል ነው ወይ??? ሎጎ የድርጅት ምልክት ቢሆንም እውነተኛው ማንነቱ ግን በህዝብ ልብ ውስጥ ነው።
ታዲያ የህዝብን ልብ የሚነካውን ምልክት መቀየር የገንዘብ ወጪ ብቻ ሳይሆን የደንበኛን ልባዊ እና ታሪካዊ ትስስር ስሜትን ማጣትስ አይደለምን?
“A logo is not what the company says it is. It’s what the people feel it is.”
Via ዮአኪን በቀለ