የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጀኔራል ታደሠ ወረደ፣ የውጭ አካላት የትግራይን ማዕድናት እየበዘበዙ ይገኛሉ በማለት ዛሬ መቀሌ ውስጥ በዘርፉ ዙሪያ በተካሄደ መድረክ ላይ መናገራቸውን የክልሉ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
ኾኖም ጀኔራል ታደሠ “የውጭ አካላት” ያሏቸውን ማዕድን መዝባሪዎች ማንነት ለይተው እንዳልጠቀሱ ተነግሯል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የማዕድናት ምዝበራን ለመከላከል ያቋቋመው ግብረ ኃይል፣ ከሰሜን ምዕራብ ዞን ብቻ 440 የወርቅ ማውጫ ማሺኖችን ከሕገወጥ የማዕድን ቦታዎች መያዙን በመድረኩ ላይ ባቀረበው ሪፖርት መናገሩን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።
ትግራይ በተያዘው ዓመት ከወርቅ ማዕድን አውጪዎች 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ትጠብቅ እንደነበር የጠቀሰው ግብረ ሃይሉ፣ በዓመቱ የተገኘው ግን 24 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ገልጧል ተብሏል።
