በሲዳማ ክልል ከሀዋሳ ወደ በንሳ ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተገልብጦ የሶስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል።
አደጋው በምስራቃዊ ሲዳማ ዞን በቦና ወረዳ ኦሎንሶ ሆሬ ቀበሌ ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ መከሰቱን የክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የመንገድ ደህንነትና ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር መለሠ ቡኑራ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-02166 የሆነው ኤፍኤስአር የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በአደጋው ተገልብጦ የሁለት ሴቶችና የአንድ ወንድ ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በቦና አጠቃላይ ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ ሲሆን፣ የተጎጂዎችን ቁጥር ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኢንስፔክተር መለሠ ጠቁመዋል።
የአደጋው ትክክለኛ መንስኤ እስካሁን ያልተለየ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም የመምሪያ ኃላፊው አስታውቀዋል።
