የሳዑዲ አረቢያ መንግስት እሁድ ሐምሌ 20, 2017 ዓ.ም. (July 27, 2025) በሶስት ኢትዮጵያውያን ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙን የሀገሪቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ቅጣቱ የተፈጸመው በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው የናጅራን ግዛት ውስጥ ነው።
በእለቱ አራት የውጭ ሀገር ዜጎች በሞት የተቀጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሶስቱ ኢትዮጵያውያን፣ አራተኛው ደግሞ የፓኪስታን ዜጋ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ በሞት የተቀጡትን ኢትዮጵያውያን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ እነርሱም፦
1ኛ. ከሊፋ ሁሴን አብዱልቃድር
2ኛ. አብዱልኑር ያሲን አደም
3ኛ. አብደላህ ኡመር ኢብራሂም መሆናቸውን ገልጿል።
ግለሰቦቹ “ሀሺሽ” የተባለውን አደንዛዥ እጽ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማስገባት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን መግለጫው አስረድቷል። በቀረበባቸው ክስም፣ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከታየ በኋላ በሞት እንዲቀጡ እንደተወሰነባቸውና፣ ይግባኝ ጠይቀው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔው ከጸና በኋላ ቅጣቱ ተፈጻሚ መሆኑን ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።
ይህ ክስተት በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመው የሞት ቅጣት አሳሳቢነቱን የቀጠለ መሆኑን ያሳያል። ከሁለት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ ወንጀል ሁለት ኢትዮጵያውያን በሞት መቀጣታቸው ይታወሳል። በእሁዱ የቅጣት አፈጻጸም፣ በ2025 ብቻ በሳዑዲ አረቢያ በሞት የተቀጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ቁጥር 105 ደርሷል።
ከዚህም በላይ፣ በአሁኑ ወቅት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ቅጣታቸው እንዲፈጸም የሚጠባበቁ ከ70 በላይ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤቶች እንደሚገኙ ከዚህ ቀደም የተዘገበ መሆኑ፣ የችግሩን ጥልቀትና አሳሳቢነት በጉልህ ያሳያል።
ሪያድ፣ ሳዑዲ አረቢያ።
(ዘ-ሐበሻ ዜና)
