ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ለሚገኙ ሁሉም ሀገራት እኩል ልማትና ደህንነትን ለማረጋገጥ “ሁሉን አቀፍ አካሄድ” ትከተላለች ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ታዬ በ80ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ቀይ ባሕርን እና ህንድ ውቅያኖስን የሰው ልጆች “የጋራ ቅርስ” ሲሉ በመግለፅ፣ ሁሉም ሀገራት እኩል ተደራሽነት እንዲኖራቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
አያይዘውም ከፍተኛ ባሕርን የሰው ልጅ የጋራ ቅርስ አድርጎ የሚገልጸው እና ሁሉንም ሀገራት በእኩልነት የመጠቀም መብትን የሚያረጋግጠው የዓለም አቀፍ ሕግ እውን መሆን አለበት ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በአዋዛ ቱርክሜኒስታን ተካሄዶ በነበረው ሶስተኛው የባሕር በር የሌላቸው በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ጉባኤ ላይ የተናገሩትን በማስታወስ፣ “አንድም ሀገር በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ምክንያት ከልማት ዕድሎች ሊገለል አይገባም” ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ለሚገኙ ሁሉም ሀገራት እኩል ልማትና ደህንነትን ለማረጋገጥ “ሁሉን አቀፍ አካሄድ” እንደምትከተል ገልፀው “ህጋዊ የፖሊሲ ግቧን በዲፕሎማሲያዊና በሰላማዊ ተሳትፎ እንደምታስቀጥል” ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛ ትልቅ የሕዝብ ብዛት ያላት እና ከፍተኛ የባሕር ንግድ ያላት እንደመሆኗ በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ ደኀንነት ላይ ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ መግለፃቸውን አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል።
addisstandardamharic
