በአትላንታ ጆርጂያ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን፤ ለ200 ታካሚዎች የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና የሚውልና 2.6 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶችን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ ፎክስ 5 አትላንታ ዘገበ።
ይህ የሕክምና ድጋፍ የሚመራው በትውልደ ኢትዮጵያዊው የፒድሞንት ሆስፒታል (Piedmont Hospital) የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ተስፋዬ ተሊላ እና በሞርሃውስ የሕክምና ትምህርት ቤት የምታገለግለው ባለቤታቸው ዶክተር ኦብሰኔት መሪድ ነው።
ህክምናው የሚከናወነው «ኅርት አታክ ኢትዮጵያ» በተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅታቸው በኩል መሆኑን የዜና ወኪሉ ጠቁሟል።
ሰባት የልብ ቀዶ ጥገና ሐኪሞች ጨምሮ ከስድስት ሀገራት የተወጣጡ 50 የሕክምና ባለሙያዎች ህክምናውን ለማከናወን ወደ ኢትዮጵያ ይጓዛሉ ተብሏል።
እንደ ፎክስ 5 አትላንታ ዘገባ፤ ይህ የበጎ አድራጎት ሥራ የተጀመረው ዶክተር ተስፋዬ ተሊላ በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩትን አጎታቸውን ኢንተርቬንሽናል ካርዲዮሎጂ ማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት በሞት ካጡ በኋላ ነው።
ዶክተር ተስፋዬ ይህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለውን የላቀ የልብ ሕክምና የማግኘት ዕድል ከፍተኛ ልዩነት ያመላክታል ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ይህ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት በከፍተኛ ሁኔታ ድጋፉን በማስፋፋት፤ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱን የነፃ ሕክምና አገልግሎት ሥራ የሚደግፉ ከ600 በላይ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንዳሉት ዘገባው አመልክቷል።
ድርጅቱ አሁን ሊሰጥ ያቀደው ሕክምና ለአመስተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሚያከናውነው መሆኑ ተገልጿል።
