በአዲስ አበባ ሕገወጥ የእንስሳት እርድና የሥጋ ዝውውርን ለመከላከል በተካሄደ ቁጥጥር 3,437 ኪሎ ግራም ሥጋ፣ 50 በግና ፍየሎች እንዲሁም 12 ሌጦዎች መወረሳቸው ተገለጸ።
የሕገወጥ እንስሳት እርድ፣ ሥጋና የቁም እንስሳት ዝውውር ቁጥጥርና መከላከል ግብረ ኃይል እንዳስታወቀው፣ በከተማዋ 604 ተቋማት ላይ በተደረገ ፍተሻ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ታርዶ ለሽያጭ የተዘጋጀው ሥጋ ተወርሷል።
በቁጥጥሩ ወቅት ሕገወጥ እርድ ሊፈጸምባቸው የተዘጋጁ 50 በግና ፍየሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ 12 ሌጦዎችም ተይዘው ወደ ሚመለከተው ተቋም ገቢ ተደርገዋል።
በተጨማሪም ሕገወጥ እርድ ፈጽመው የተገኙ 49 ድርጅቶች ለጊዜው የታሸጉ ሲሆን፣ ቅጣታቸውን ከከፈሉ በኋላ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንዲከፈቱ መደረጉ ተጠቁሟል።
ቁጥጥሩ የተካሄደው የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን፣ የንግድ ቢሮ፣ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እና የአዲስ አበባ ቄራ ድርጅት በጋራ በማስተባበር ነው።
