በእርጋታ መፍጠን ይቻላል

Date:

 

 ከዕዝራ እጅጉ

ግዮን መጽሔት :-    ሕይወቴ በእርጋታም በፍጥነት የተሞላች ነች፡፡ ስረጋጋም ሰላም አገኛለሁ ፈጥኜ ስደርስም ርካታዬ ያይላል፡፡ በዘመኔ የተረጋጋሁ ሰው የሆንኩበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ችኩል ነህ ስባል  ነው ያደግኹት፡፡ መዘግየት አይሆንልኝም፡፡ ቶሎ ማጠናቀቅ ይሳካልኛል ብቻ ሳይሆን የተፈጠርኹትም ቶሎ ለመፈፀም እንደሆነ አድርጌ አስባለሁ፡፡ እያነበብኩ ስመጣና ሕይወት ጥበብ እየለገሰቺኝ ካስተማረቺኝ በኋላ በ40 አመቴ ልብ አስገዛቺኝ፡፡ አሁንም ልብ ገዝቼ ተረጋግቼም እፈጥናለሁ፡፡ ፍጥነቴም ለራሴ እያስደነቀኝ ተመስገን ጌታ ሆይ ለማለት እሻና የሀይስኩል ጋይዳንስ ካውንስለራችን ከፊቴ ድቅን ይላል፡፡ ‹‹ልብህ ተራራ ቢሆንም ግን አትቸኹል›› እያለ ሥነ ልቦናዊ ምክሩን ከልቡ ይለግሰኝ ነበር፡፡ እና ስፈጥን እሰጋለሁ፡፡ መስከኔ የሚወሰድብኝ እየመሰለኝ፡፡

ቶሎ ማሰብ፣ ቶሎ መፈፀም ዛሬ ያሰብኩትን ነገ ሳልቀደም ተግባራዊ ማድረግ ልማዴ ሆነና 47 ዓመቴ ላይ ደረስኩ፡፡ እዚህ ምድር ከመጣሁ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሊሞላኝ 36 ወራት ይቀራሉ፡፡ አሁን ደግሞ የተገለጠልኝ እውነት የወዳጄ የዘሪሁን አሰፋ በእርጋታ መፍጠን የሚለው እሳቤ ነው፡፡እየረጉም እየፈጠኑም መጓዝ እንዴት እንደሚቻል ስጠይቅ ሳሰላስል ኖሬ አንዴ ስተገብረው ሌላ ጊዜ ሲያቅተኝ እንደ መርህ ግን ልከተለው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አምኜ በአዲሱ ዓመት ልረጋና ልፈጥን – ሁለቱን አጣምሬ ልነጉድ ተዘጋጀሁ፡፡

አእምሮዬ ሲፈጥን፣ ሲያስተውልና ወደ ድርጊት ቶሎ ሲያራምደኝ ድንቅ ይለኛል፡፡ በጣም ስረጋጋ፣ ስታገስ፣ ተወት ሳደርግ ነገሮች በራሳቸው መሳካት ጀመሩ፡፡ በእርጋታ መፍጠን እንዴት እንደጠቀመኝ ልጠቋቁም ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ብቅ ያልኹት፡፡

እኔ ፈፅሞ ሳላዘው አእምሮዬ የሆኑ ነገሮችን ፈጥኖ  ያስባል፡፡ ከቁጥጥሬ ውጭ በሆነ መንገድ አዳዲስ ሀሣቦች ይፈልቃሉ፣ ሀሣቦች ይወጣሉ – ይወርዳሉ፡፡ ውስጤ በራሱ ይነቃቃል፡፡ ከዚያ ደግሞ ማስተዋል፣ መብሰል እንዳለበት ሳስብ አሰክነዋለሁ፡፡ ግን እንደሰከነ አይቀርም፡፡ ደግሞ አፈጥነዋለሁ፡፡ በእርጋታ መፍጠን ማለት እያስተዋሉ መሮጥ መርጋትንም መፍጠንንም በተመሳሳይ ሰዓት ገቢራዊ ማድረግ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ  ጊዜ ብዙ (በቁጥር) ሥራ ግን ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ነገር  ማበርከቴ  በእርጋታ ስለፈጠንኹ ይሆን? ብዬ አስባለሁ፡፡ ይመስለኛል፡፡

እርጋታዬ ምንድነው?

ከላይ እንዳልኳችሁ በልጅነቴ ችኩል ነበርኹ፡፡ አሁን እየኖርኹበት ያለው የመረጋጋት ዘመን ግን ከተሞክሮና በእድሜ የመጣ ነው፡፡ እርጋታዬ ልክ እንደ ሙቅ ውሃ ችኮላዬ ላይ ሲበረዝ ሚዛኑን የጠበቅኩ ኖርማል  እሆናለሁ፡፡ የሚፋጅ እሳት በቀዝቃዛ ውሃ ሲበረዝ እንደሚረጋጋው እኔም እረጋጋለሁ፡፡ እኔ ሙቅ ውሃና ቀዝቃዛ የተቀላቀለብኝ ውሃ ነኝ፡፡ አዋጥቶኝ ትርፋማ አድሮጎኝ፣ በአዲሱ ዓመት ደግሞ ማስተዋሌን ዳግም እያደስኩ እርጋታዬን እየተንከባከብኹ እገኛለሁ፡፡እርጋታዬ እንዳይወሰድብኝም እፀልያለሁ፡፡

የምር ግን እርጋታዬ ምንድነው? እንዴት ቻልኹበት? የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል እንዲሉ ለእኔም አንዳንድ ነገሮችን መታገሴ እጅግ ጠቅሞኛል፡፡ ከራሴ ተሞክሮ ሳካፍል  ከደመ ችኩልነት ወደ ደመ መረጋጋት ዘመን ስሸጋገር ነገሮች መልካም ይሆኑልኛል፡፡

መቀመጥን የመሰለ ምርጥ ነገር የለም፡፡ በተለይ ለመረጋጋት ፀጥ ያለ ቦታ ላይ ሁኖ ማሰብ ያበስላል፡፡ ለመረጋጋት መለማመድ ያስፈልጋል፡፡ የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል እንዲሉ መረጋጋትን እንደ ሰውነት  እንቅስቃሴ ለውስጣችን ካላስለመድነው በቀላሉ cool የሚለውን ማዕረግ አናገኝም፡፡

ወዳጄ ዘሪሁን እንዲህ ይላል፦ ‹‹ልረጋጋ ወይስ ልፍጠን ተቃርኖውን በፍጥነት እና በእርጋታ መካከል በመኾን ማስታረቅ ይቻላል፡፡ የመሀሉን መንገድ መከተል ነው፡፡

በእርጋታ መፍጠን!

Strive for perfection, while your talents are still blooming.

ከአዲስ ዓመት በፊት ጷጉሜን የምወዳት የአገራችን መሸገገሪያ ወር ብቻ ስለኾነች አይደለም፡፡ መስከረምን ስለምታጎናጽፈን ነው፡፡ በጸሎት የከርሞውን ዘመን በመመልከት መጪውን ደግሞ በተስፋና በአዲስ እሳቤ መጓዝን ለማንጸር ይኾናል፡፡ እርጋታ የሚመጣው በመፍጠን ብቻ አይኾንም፡፡ ስኬታማ ሥራን ለማከናወን በመሀል መኾን ይጠቅማል፡፡›› ሲል ዘሪሁን አስተሳሰቡን ያሰርፃል፡፡ የእውነትም ደስ የሚል እሳቤ ነው፡፡

በእንግሊዝኛውም “Great success is born from a free mind, not a busy schedule”. ብሎ ያምናል ዘሪሁን፡፡

ሚዛን አስፈላጊ ነው፡፡  ዘሪሁን እሳቤውን አፍታቶ ሲያቀርብ፦

‹‹…..ከአዲስ አበባ ሊመሽ ሲል ግድም ወደ ሀዋሳ ጉዞ ብንጀምር እንዴት ነው አካሄዳችን? በሰዓት 60 ኪ.ሜ. ስንጓዝ ደንገዝገዝ እያለ ቢኾን ትንሽ ፍጥነት ጨመር እናደርግና በሰዓት 90 ኪ.ሜ. እንነዳለን፡፡ ከዚያ ካለፈብን ፍጥነቱን መቆጣጠር አንችልም፡፡ የሀዋሳ መንገድ ደግሞ በአብዛኛው ሜዳማ ነው፡፡ ውጥረትና ፋታ የማይሰጥ መንገድ ነው፡፡ ታዲያ ከዘገየን ከቀን ውጭ የሚፎንኑ ሰውና ፍጡራን ይነግሱበታል፡፡ በመኾኑም በሰዓት 120 ኪ.ሜ. ከመሄድ በእርጋታ እየፈጠንን ተጉዘን ያሰብንበት እንደርሳለን፡፡

የቀን ውሏችን ከምሽት አራት እስከ ስድስት ሰዓት ይጠናቀቃል፡፡ በዚህ ጊዜ የቀኑ ፈጣሪ፣ ሊቁና ኢንጂነሩ ቀመር ከቀን የሰውነት ቅመሞች ወደ ሌሊት እንቅልፍ የሚቀየሩበት ነው፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ቢኾንም አዋቂዎቹ እንደሚሉት በዚህ ጊዜ መተኛትና በማለዳ መነሳት ከተፈጥሮ ኡደት ጋር መጓዝ ስለሆነ ጤናማ ያደርጋል፡፡ ታዲያ ተፈጥሮስ በእርጋታ መፍጠንን አያሳየንም?›› ይላል ዘሪሁን ገላጭ በሆነ መልኩ ሀሣቡን ሲያስቀምጥ፡፡

‹‹…..እኛ ደግሞ ተንቀሳቃሽ ፍጡራን ስለኾንን መፍጠን እና መዘግየት ይገጥመናል፡፡ በተለያየ ምክንያት የሚገጥመንን ኹነት አስተውለን በእርጋታ መፍጠን ስንችል ተፈጥሮአችንን እንጠቀማለን፡፡ በእርጋታ መፍጠን አትራፊ ያደርጋል›› ሲል ዘሪሁን ሀሣቡን ቋጭቶ ያስቀምጣል፡፡

ከእኔ የባሰ cool ሰው ሳይ እቀናለሁ፡፡ ሲራመድ በእርጋታ፣ ሲያነብ በእርጋታ፣ ሀሣቡን ሲያብራራ በእርጋታ፣ ሲናደድ በእርጋታ መቼ ነው እኔም ወደዚህኛው ወንዝ የምፈሰው እያልኹ እንደዛ መሆንን እናፍቃለሁ፡፡

የቱንም ያህል ሥራ ቢበዛብኝ በተለይ ዘንድሮ በማረፍ፣ በመስከን እና ባለመባከን ነው ያሳለፍኹት፡፡ መረጋጋቴ ሲጋነን ደግሞ  የመቆጨት ስሜት ውስጤ ይሰነቀርና  ደግሞ መሮጥ ይከተላል፡፡ ስረጋጋ ስህተት ከመስራት እድናለሁ፡፡ ስረጋጋ  ጭንቀት ልቅቅ ያደርገኛል – ከዚያም ኃይሌ ይታደሳል፡፡ ኃይሌ ሲታደስም ውስጤ ያለውን እምቅ አቅም ማውጣት እጀምራለሁ፡፡

መፍጠኔ ለምን ነው?

ነገሮችን ሳልሠራቸው ጊዜ የሚያልፍብኝ ይመስለኛል፡፡ መቀደም አልወድም፡፡ የማስበውን ነገር ቶሎ ካልተገበርኹት  ሰላሜ ይነሳል፡፡ በዕድሜዬ መጠቀም እንዳለብኝ አስባለሁ፡፡ ሥራዬ ወይም በየጊዜው የምፈጥራቸው ነገሮች ትምህርት ቤቶቼ ስለሆኑ የትምህርት ቤት ጊዜዬ እንዳያልፍ  እጣጣራለሁ፡፡ በትኩስ ጉልበቴ አሁን፣ በቶሎ መስራት እንዳለብኝ አስብና እፈጥናለሁ፡፡ ፍጥነቴ ተፈጥሮዬ ስለሆነ ራሴን ሆኜ በመገኘቴ እደሰትና ግን ደግሞ በችኮላ የምሠራቸው ስህተቶች ወይም ግድፈቶች ተፈጥረው አያቸዋለሁ፡፡ እርግጥ ነው መፍጠኔ ሸጋ ነው ቢባልም አለመስከን  ያመጣብኝ ጣጣ ዋጋ ያስከፍለኛል፡፡ በመሆኑም ፍጥነትን የምተወው ሳይሆን ከመረጋጋት ጋር የማስኼደው ነው፡፡ በፍጥነቴ የሚወቅሱኝን ሰዎች ሙሉ ለሙሉ አልሰማቸውም፡፡ መፍጠኔ፣ ያበረከተው ነገር አለና እሱን ይዤ እቀጥላለሁ እላለሁ፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም  2019 ዓ.ም

 

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

‹‹ግዮን›› ጥሪዋን ታቀርባለች!

ግዮን መጽሔት :-    በየዓመቱ የዘመን መለወጫን ስናከብር የቀደመውን...

የ1987ቱ ሕገ-መንግሥት የብዝኃነት ተስፋ ወይስ የልዩነት ማኅፀን?

  በዮሐንስ ይባቤ ተስፋይ (ፕ/ር) ግዮን መጽሔት :-  የ1987ቱ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት...

ኢራን የድርድር ዕቅዷን ለአሜሪካ ልካ ምላሽ እየጠበቀች ነዉ

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፣ አገራቸው ሰባት ነጥብ...