ጠበቃ መሠረት ሥዩም ( የማኩታ የሕግ አገልግሎት መሥራችና ማኔጂንግ ፓርትነር )
በክፍል ሁለት ለጠበቃ መሠረት ያነሳናቸዉ ጥያቄዎች አነዚህን ይመስላሉ – ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ትልልቅ የውጭ ተቋማት ጋር ያላችሁ የሥራ ግንኙነት ምንድን ነው? – በሀገራችን በርካታ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ተሳትፎ ነበረሽ? – ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበራት አባል ናችሁ? በነዚህና በሌሎች ጥያቄዎች የነበረንን ቆይታ ተከታተሉት።
ግዮን መጽሔት :- ከአገር ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ የነበረሽ የሥራ ልምድ የት ነው?
መሠረት፡- ወደ ደቡብ ሱዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የወሰደችኝ አንዲት ሴት ናት፡፡ በጉዞ ላይ እያለን በአውሮፕላን ውስጥ ከአንድ ትልቅ ድርጅት ባለቤት ጋር ተዋወቅን፡፡ ድርጅታቸው የዳታ ቤዝ ሲስተምና ኤሮስካን በዚህ ጉዳይ እያወራን እኔ መሥራት እንደምችል ነገርኩት፡፡ የሄድኩትም ገና በአፍላ ወጣትነቴ ነው፡፡
በጣም ደፋር ነኝ፣ ነውርን ግን አልደፍርም፡፡ ከነውር በስተቀር ሌሎችን ለመድፈር ችግር የለብኝም፡፡ ሥራውን ለመሥራት ተስማምተን ብንጀምርም፣ ለመሥራት ግን በጣም ተቸገርኩ፡፡ የአንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሚስት አፈላልጌ አገኘኋት፡፡ እሷም እንደ ኮንሶልታንት (አማካሪ) ትሠራ ነበር፡፡ የሥራውን ሁኔታ በዝርዝር ነገርኳት፡፡
‹‹አብረን እንስራ፣ ክፍያውን አንቺ ተጠቀሚ እኔ አልፈልግም›› አልኳት፡፡ እሷም ግራ ገብቷት ድፍረቴና ያቀረብኳቸውን ሐሳቦች ተረድታ ‹‹እሺ›› አለችኝ፡፡ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ሁሉ አመቻቸችልኝ፡፡ ወደ ሚመለከተው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ሔድኩኝ፡፡ በሥራ ደረጃ የመጀመሪያ ከሃገር ውጭ የሰራሁት ደቡብ ሱዳን ነው። ለደቡብ ሱዳን መሥራት ይፈለግ ነበር።
ሥራው በጣም አድካሚ ነበር፡፡ ነገር ግን በብዙ ልፋት ሥራው ተሳክቶ ድርጅቱም አስፈላጊውን ውል ፈርሞ፣ የሚያስፈልገውን ሥራ ተረክቦ ሰራ። ለእኔም በውሉ መሰረት ክፍያውን በአግባቡ ከፈለ። እኔም ሙሉ ክፍያውን ወስጄ አስረከብሁ። ማለትም ውሉን በእርሷ አማካሪ ድርጅት ስለሆነ ያደረግሁት፣ ወደ እሷ ኩባንያ ክፍያው እንዲገባ ሆነ፡፡
እኔም ሥራውን በማሳካቴ ደስ አለኝ። እሷ ግን ስላልጠበቀች በጣም ግራ ገባት፡፡ “አንች እኮ ነሽ የሰራሽው” አለች። በፍጹም ሥራውን እንደማሳካው አልጠበቀችም። በመጨረሻም ይህ የአንቺ ድርሻ ነው ምንም እንኳ ክፍያውን ሙሉ ውሰጂ ብለሽኝ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን 30 ፐርሰንት አንች መውሰድ አለብሽ ብላ 30 ፐርሰንት ሰጠችኝ።
ግዮን፡- ይኽን ክፍያ ከተቀበልሽ በኋላ ወደ ምን ሥራ ተሠማራሽ?
መሠረት፡- ወደ ዑጋንዳ ሔድኩና ድንኳኖች አመጣሁ፡፡ ከአንድ ሰው ጋር ቦታ ተከራየን፣ ኤሲ አስገባን፣ ፈርኒሽ አስደረግን፣ ድንኳን እንደ ሠርተን ማከራየት ጀመርን፡፡ በቀን 300 ዶላር እናከራያለን፡፡ ገስት ሀውስ ገዝቶ ማከራየት፣ የትልቅ ፕሮዳክት ኤጀንት ኾኖ መሥራቱንም ተያያዝኩት፡፡ ያኔ ኤሲ የለም፤ በቬንቲሌተር ነበር የሚሠራው፡፡ ዳሩ ግን ከሥራ ያልተለየ አስተዳደግ ስለነበረኝ የነበሩት ከፍታና ዝቅታዎች አላወኩኝም፡፡
በሒደት እዛ ካለው የሕግ ድርጅት ጋር ግንኙነት ጀመርን፡፡ ሥራዎችም ያመጡልኝ ነበር፡፡ በሀገር ውስጥ ካሉ የሕግ ባለሙያዎች ጋር ተጣመርኩ፡፡ አዲስ ሀገር እንደመኾኑ ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ ረዳኝ፡፡ በተጨማሪም በሙያዬም በደንብ ሠርቼበታለሁ፡፡ ከኢንተርናሽናል የሕግ ባለሙያዎች ጋር ለመገናኘትም ድልድይ ኾኖኛል፡፡
ግዮን፡- በደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያውያን ጋር የነበረሽ ግንኙነት ምን ይመሥል ነበር?
መሠረት፡- ኢትዮጵያውያን ለደቡብ ሱዳን ባለውለታዎች ናቸው፡፡ የእኛ ልጆች እዚያ በጣም ነው የሚሠሩት፡፡ እኔም እዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መርዳትና በሥራ ማቋቋም እጅግ ያስደስተኝ ነበር፡፡ ስማቸውን አሁን መጥቀስ የማልፈጋቸው ያኔ የረዳኋቸው ትልቅ ደረጃ የደረሱ ሰዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ከባንክ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ገጥሞት ነበር፡፡
ወደ እኔ መጥቶም ‹‹ከሰርኩኝ›› አለኝ፡፡ እኔም የሚፈልገውን ኩባንያ አቋቋምኩለት፡፡ ልጁም በጣም ጎበዝ ስለነበር ወዲያው ተለወጠ፡፡ አሁን ወደ ሀገሩ ተመልሶ የዘይት ፋብሪካ ከፍቷል፡፡ አስገራሚ ሕንፃም ገንብቷል፡፡ ከ3ሺ ሄክታር በላይ የሰሊጥ እርሻም አለው፡፡ በዚህ መልኩ ያገዝኳቸው እኔንም ያገዙኝ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡
ደቡብ ሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤንባሲ ባለሥልጣንም ‹‹አግዣቸው›› እያለ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ወደ እኔ ያመጣቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ አሁን ስሙን የማልጠቅሰው በጣም እንደ ወንድሜ የምወደው ጎበዝ ልጅ ነበር፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ሳውቀው በደቡብ ሱዳን በሚገኝ ባንክ ውስጥ ነው ያገኘሁት፡፡ ከኢትዮጵያ እንደወጣ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ስራ እንደነበረው፣ ኾኖም እንደከሰረ 50 ሺህ ብር ብቻ ይዞ እንደመጣ አጫወተኝ። እኔም እንደማግዘው ነገርሁት፡፡ ኩባንያ እንዲያቋቁም እና እንዴት ሕጋዊ መስመር አስይዞ እንደሚሰራ አማከርሁት፡፡ አቅጣጫ አሳየሁት ፤ አገዝሁት። እሱም ጎበዝ ስለሆነ በቀላሉ ወደ ሥራ ገባ።
በየጊዜው የሚፈልገውን አማክረው ነበር። በፍጥነት ነው ሰርቶ የተለወጠው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የፋብሪካና የእርሻ ባለቤት ነው፡፡ በአስመጪና ላኪነትም ዘርፍ የተሣካለት ነጋዴ ሆኗል፡፡ በዚህም መልክ ያገዝኳቸው በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ የነበሩ መሪ የተቸገሩ ሰዎችን እንዳግዛቸው ይልኳቸው ነበር፡፡ እኔም ደስ ብሎኝ ነበር የማግዘው፡፡
በሀገሪቱ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ኢንቨስተሮችንና ከሀገሪቱ ኮሜርሻል ነክ ውሎች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በመሥራት ከፍተኛ ሚና ነበረኝ፡፡ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍም ተቋማት ተግባብተው እንዲሠሩ በማደረግ በኩል የራሴ ሚና ነበረኝ፡፡
ደቡብ ሱዳን እንደሁለተኛ ሀገሬ ነው የምቆጥራት፡፡ በቀውስ መታመሷን ተከትሎ ብዙ ባልሄድም አሁንም ድረስ ግን በርካታ ሥራዎችን እሠራለሁ፡፡ 18 ክፍል ያለው አንድ ገስት ሀውስም አለን፡፡ እዚያ ካሉ የሕግ አካላት ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥ ዓለም አቀፍ ሕግን የተመለከቱ ጉዳዮች ሲኖሩም በጋራ እንሠራለን፡፡
ደቡብ ሱዳን ሙያዬን ያሳደግኩባት ሀገር ናት፡፡ በጥቅሉ ከደቡብ ሱዳን የተነሳው የሕይወትና የሥራ ጉዞዬ እንደ ዑጋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ጋና፣ ኮትዲቫር፣ ሞሪሺየስ፣ ሲሸልስና ሌሎች ሀገራት የደረሰ ነው፡፡
ግዮን፡- ‹‹ማኩታ›› መቼ ተመሠረተ? ምንስ ማለት ነው?
መሠረት፡- “ማኩታ” የሚለው ቃል አማርኛ ነው፡፡ ቃሉን የከሳቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት ‹‹ተስፋ፣ አለኝታ ወይም መከታ ማለት ነው›› ብሎ ይተረጒመዋል፡፡ የተመሠረተው በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2023 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን በዚህ ቅርፅ ባይኾንም ‹‹መሠረት የጥብቅና ማኅበር›› በሚል ለ15 ዓመታት ሠርተንበታል፡፡
ግዮን፡- ድርጅታችሁ በውጪ ሀገራት ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉት?
መሠረት፡- አዎ! ቻይና እና ዱባይ ላይ አለን፡፡ በተጨማሪም በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ከፍተናል፡፡ ስምምነቶችንም በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ አሁን አፍሪካ ውስጥ አሥራ ስምንተኛ ቅርንጫፍ አሁን እየከፈትን ነው፡፡ ብዙ አፍሪካ አገራት ገብተን ለመሥራት እድሉን የከፈተልን የአሠራራችን ሂደት ከሌላው ለየት ያለና ከተመለመደው ወጣ ያለ በመኾኑ ነው፡፡
ይህም ማለት እኛ ዋና ኾነን የውጭ አካላትን በታችኛው እርከን ላይ በማሠማራት ሥራዎችን የማከናወን አሠራርን ይዘን በመምጣታችን ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የተለመደው ነጮች በበላይነት የሚመሩት ተቋም ውስጥ ጥቁሮች ዝቅ ብሎ መሥራት ነው፡፡ እኛ ይኽንን መንገድ በመስበር ላይ እንገኛለን፡፡
ግዮን፡- ከሰዎች ጋር ያለሽ የመግግባት ችሎታ የፈጠረልሽ የተለየ አቅም አለ?
መሠረት፡- አባቴ ‹‹ሰው ሀብት ነው›› ይለኝ ነበር፡፡ ‹‹መሬት ላይ ስትወድቂ መቶ ብር ከኪስሽ ወድቆ ዘሎ አያነሳሽም፡፡ መጀመሪያ የሚያነሳሽ ሰው ነው›› ይለኝ ነበር፡፡ እኔም ሰው ሀብት መኾኑን በደንብ ተረድቻለሁ፡፡ በጉዞና መሠል አጋጣሚዎች ሁሉ የማገኛቸውን ሰዎች በአግባቡ ነበር የምይዘው፡፡ ለሥራዬም ትልቅ ድልድይ ኾነውልኛል፡፡
ከእኔ ጠና ያሉ፣ በእውቀትም ይሁን በእድሜ የገፉ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለእኔ በርካታ የሥራ እድል ፈጥረውልኛል፡፡ በዚህ የሥራዬ አጋጣሚ በርካታ የአፍሪካ መሪዎችንም ለማወቅ ችያለሁ፡፡ እነርሱም እኔ ማንና ምን እንደኾንኩ በሚገባ ማወቅ ችለዋል፡፡ ይኼ ደግሞ በሀገራቱ ተዘዋውሬ ሥራ ለመሥራት እንግዳ እንዳልኾን አድርጎኛል፡፡
በሥራዬም ሰዎችን መርዳት ያስደስተኛል፡፡ ይህንንም ከአባቴ ተምሬያለሁ፡፡ አባቴ ለእሱ ልብስ ሳይገዛ ለእናታችን ገዝቶ መጥቶ እሷ ለብሳው ሲያይ በጣም ይደሰታል፡፡ እኔም ሰዎች ስኬታማ ሲኾኑ ደስ ይለኛል፡፡ ይህ ባሕሪዬ ከሰዎች ጋር ለመግባባት ጠቅሞኛል፡፡ በሥራዬ የመታመን ዕድልንም አካብቶልኛል፡፡
ማስታወሻ- ውድ አንባቢያን፣ ከጠበቃ መሠረት ሥዩም ጋር ያደረግነው ቆይታ ክፍል ሦስት በሚቀጥለው ቀናት ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡
