አንድ ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ አማካሪ በድጋሚ አሜሪካ ቴህራን ላይ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ አዲሱ ጦርነት እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ሊሰፋ እንደሚችል አስጠነቀቁ።
የኢራን የወታደራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ መሪ ከፍተኛ አማካሪ ሜጀር ጄኔራል ያህያ ራሂም ሳፋቪ ሐሙስ ዕለት የአገሪቱ የጦር ኃይል ለተለያዩ ሁኔታዎች ዕቅዶችን አዘጋጅቷል ማለታቸውን የፋርስ ዜና ወኪል ዘግቧል።
ሳፋቪ “በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና እስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አእምሮ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ አናውቅም” ብለዋል።
የኢራን ጦር በአገሪቱ ተቋማት ወይም ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ተጨማሪ የአሜሪካ ወይም የእስራኤል ጥቃቶች ቢከሰቱ በሚል ለከፋ ሁኔታዎች መዘጋጀቱን ገልጸው፣ ግጭቱ ሊሰፋ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
“አሁን ጦርነቱ ከባህር ሰላጤው እና ከሆርሙዝ ወሽመጥ ወደ ቀይ ባህር ተስፋፍቷል። ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ቀጣይ ጦርነት ወደ ሕንድ ውቅያኖስ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሊሰፋ ይችላል” ብለዋል።
