የጽሁፍ አዘጋጅ ታደሰ ብሩ (ዶ/ር)
ግዮን መጽሔት :- የብሄር ግጭት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም፣ በሃይማኖት ሽፋን የሚደረጉ የዲጂታል ቅስቀሳዎችም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መጥተዋል። የሃይማኖት እና የቴክኖሎጂ መስተጋብር በኦርቶዶክስ፣ በሙስሊም እና በፕሮቴስታንት ወጣቶች ዘንድ “ራስን የመከላከል ሃይማኖተኝነትን” (Defensive religiosity) ፈጥሯል።
ማኅበራዊ ሚዲያው የሃይማኖት ተቋማትን መዋቅራዊ ተዋረድ አፍርሶታል። ወጣት እና አንደበተ ርቱዕ የሆኑ የኦንላይን ሰባኪዎች እና የእምነት ተከራካሪዎች ብዙውን ጊዜ የሃይማኖትን ተቋማዊ አመራር (ሲኖዶስን፣ መጅሊስን ወይም ጉባኤዎችን) በመተላለፍ ጽንፍ የለቀቁ ትርጓሜዎችን ያሰራጫሉ።
በተቋማት ውስጥ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ማኅበራዊ ሚዲያው እነዚህን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ወደ ግጭት መለኮሻነት ይቀይሯቸዋል።
“የሞራል ድንጋጤዎች” (moral panics) በእነዚህ መረቦች ውስጥ በፍጥነት ይሰራጫሉ። አንዱ የእምነት ቡድን ሌላውን “ለማጥፋት” ወይም “ለመቆጣጠር” አስቧል የሚሉ የሴራ ትንታኔዎች በቴሌግራም ቻናሎች እና በዋትስአፕ ግሩፖች ይናፈሳሉ።
በዚህ ዘርፍ የሚደረጉ የወጣቶች እንቅስቃሴዎች ብዙውን ጊዜ “መንጋውን የመጠበቅ” ቅዱስ ተግባር ተደርገው ይወሰዳሉ። ሆኖም፣ ይህ አይነቱ ዲጂታል ቅንዓት ብዙውን ጊዜ ሃይማኖታዊ ጥልቀት የጎደለው በመሆኑ፣ ለዘመናት የቆየው የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች አብሮነት እሴት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል።
በምርጫ እና በተጽዕኖ መሃል፡ “የላይክ” ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ
በማኅበራዊ ሚዲያ እና ቅራኔዎች መካከል ስላለው ትስስር ሲጠና ወጣቶች የአልጎሪዝም ሰለባዎች ብቻ አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው። ወጣቶች በዲጂታል ተሳትፎአቸው ውስጥ የራሳቸው የመወሰን አቅም (agency) አላቸው፤ ነገር ግን ይህ አቅም የሚተገበረው በተጋላጭነት አውድ ውስጥ ሆነው ነው።
የዲጂታል ተሳትፎዓቸውን ማሳደግ የሚፈልጉ ወጣቶች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ “የላይክ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ” (The political economy of clicking) ተጽዕኖ ስር ይወድቃሉ።
ሥራ አጥነት በተስፋፋበት ሁኔታ፣ ዲጂታል አክቲቪዝም ለወጣቶች ስነ-ልቦናዊ እርካታን ብቻ ሳይሆን ለአንዳንዶች የኢኮኖሚ እድልም በመሆኑ በአስተማሪነት ይልቅ የተሻለ ዝናና ገንዘብ ወደሚያስገኝ ይዘት ለመሸጋገር ይደፋፈራሉ።
በዩቲዩብ የሚገኝ ገቢ (monetization) ወይም ለፖለቲካ ልሂቃን እንደ “ዲጂታል አርበኛ” በማገልገል የሚገኝ ጥቅም፣ ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶችን ለማምረት የገንዘብ ማበረታቻ ይሆናል። በዚህም መሠረት የማኅበራዊ ሚዲያ “አርበኛ” – ከሀገር ውስጥም ሆነ ከዲያስፖራ – የወጣቱን ብስጭት ወደ ገንዘብ ይቀይራል።
በአስተዳደር በደል፣ በሥራ ክፍያ ማነስ እና ፍትህ እጦት የሚነሱ ትክክለኛ ጥያቄዎችን የበለጠ ተከታይና ወዳጅ (like) ወደሚያስገኙ ወደ ብሄር ወይም ሃይማኖት ጥላቻ ይቀይሩታል። በዚህም ወጣቶች ድርብ ሰለባ ይሆናሉ – በአንድ በኩል ፍትሃዊ ጥያቄዎቻቸው ፍትሃዊ ምላሽ የማግኛ መንገድ ይዘጋባቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለዲጂታል እና አካላዊ ግጭት ይጋለጣሉ።
ወሳኝ የሆነ የዲጂታል ክህሎት (Digital literacy) አለመኖር ወጣቱን ለሀሰተኛ መረጃዎች ተጋላጭ ያደርገዋል። በፌስቡክ ላይ የሚሰራጭን ተራ የጥላቻ ቅስቀሳ ከታማኝ ዜና መለየት አለመቻል፣ መረጃዎች ሂሳዊ እይታን (Critical thinking) አልፈው ቀጥታ ስሜታዊ እና አካላዊ ምላሽ እንዲሰጡ ምክንያት ይሆናል።
—
ይህ ጽሁፍ በYCDF የሰላም እና ግጭት ማስወገድ መምሪያ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው። የጽሁፍ አዘጋጅ ታደሰ ብሩ (ዶ/ር) የYCDF የፕሮግራምና አጋርነት ክፍል ኃላፊ ናቸው። በ info@ycdfet.org ወይም tkersmo@yahoo.com ይገኛሉ።
ከዲጂታል ጽንፈኝነት ወደ ሰላም፡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ( በሚለዉ የተዘጋጀውን ፁሑፍ የመጨረሻው ክፍል በነገዉ ዕለት ይጠብቁን)
