እስራኤል አፍሪካውያን ስደተኞችን ገንዘብ ከፍላ ከሀገሯ ለማስወጣት አቀደች

Date:

እስራኤል ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያበረታታ የገንዘብ ድጋፍ መርሐ ግብር ማስፋፋቷ ተገለጸ።

የእስራኤል የሕዝብና የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን ባስተዋወቀው በዚህ የተሻሻለ መርሐ ግብር፣ መስፈርቱን የሚያሟሉና በፈቃደኝነት ለመመለስ የሚስማሙ ሰዎች ለእያንዳንዳቸው 3,500 የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍና በመንግሥት ወጪ የሚሸፈን የአውሮፕላን ትኬት ያገኛሉ።ከዚህም በተጨማሪ የጉዞ ሰነዶችን ለማዘጋጀት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውና እስከ በረራቸው ድረስ እስከ ሁለት ሳምንት ለሚደርስ ጊዜ ከኢሚግሬሽን እስር ጥበቃ እንደሚያገኙ ተገልጿል።

መርሐ ግብሩ ከዚህ ቀደም በዋናነት ከኤርትራ፣ ከሱዳንና ከኢትዮጵያ የመጡ ዜጎችን ያካትት የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች እንዲያካትት መስፋፋቱ ተመልክቷል።

የመርሐ ግብሩ መስፋፋት በፈቃደኝነት ከእስራኤል የሚወጡ ስደተኞች ቁጥር በ2025 ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ20 በመቶ ገደማ በመቀነሱ ጋር ተያይዞ መሆኑ ተገልጿል።

በ2024 በመርሐ ግብሩ 3,511 ሰዎች ከእስራኤል የወጡ ሲሆን፣ በ2025 ቁጥሩ ወደ 2,815 ዝቅ ብሏል። ለቅናሹ እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት መካከል በካናዳ የጥገኝነት ኮታ መቀነስ፣ በአሜሪካ የድንበር ቁጥጥር መጠበቅና በቀጣናው የበረራ መስተጓጎሎች ይገኙበታል።

የተሻሻለው መርሐ ግብር እስከ ታኅሣሥ 22 ቀን 2019 ዓ.ም. (ዲሴምበር 31 ቀን 2026) ድረስ ብቻ የሚቆይ በመሆኑ፣ በመርሐ ግብሩ መካተት የሚፈልጉ ሰዎች ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በፊት ማመልከቻቸውን ማስገባት ይጠበቅባቸዋል።

የመርሐ ግብሩ መስፋፋት በእስራኤል የሚኖሩ የአፍሪካ ዜጎችን የሚመለከት የኢሚግሬሽን ፖሊሲ ለውጥ ነው። በመሆኑም በመርሐ ግብሩ ለመጠቀም የሚያስቡ ሰዎች የተጠቀሱትን መስፈርቶችና የመመለሻ ሁኔታዎች ከእስራኤል የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን በቀጥታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተሰረቀ ዕቃ በቅናሽ ዋጋ መግዛት ወይም ይዞ መገኘት እስከ 3 ዓመት እስራት ያስቀጣል

በርካሽ ዋጋ የተሰረቁ ስልኮችን፣ ላፕቶፖችንና ሌሎች ዕቃዎችን መግዛት፣ የተሰረቀ...

በኢትዮጵያ በዓመት ከ18ሺህ በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር ይጠቃሉ ተባለ

ጤና ሚኒስቴር  ከለሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የጡት ካንሰር...

35ኛው ዓለም አቀፍ የስኳር ህመም ቀን ተከበረ

በዝግጅቱ ላይ የስኳር ህመምን ለመከላከል ቅድመ ምርመራን፣ ጤናማ አመጋገብንና...

በኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማእከል

መገናኛ ብዙሃን ሕጋዊ እና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ...