በሲዊዘርላንድ በተለያዩ አብያተክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን በህብርት ከዚህ ቀደም በሰይፉ ሾው የገቢ ማሰባሰቢያ ቀጥታ ሥርጭት አማካኝነት 7,358,900 ብር የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ይሄንኑ የተለያዩ አብያተክርስቲያናት ያደረጉትን ድጋፍ በመመልከት አሁን ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ በሲውዘርላንድ የባዝል ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንና ሌሎችም ምዕመናን በመተባበር የ 1,142,100 ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል ፡፡
ይህም በሲውዘርላንድ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን እስካሁን ያደረጉት የገንዘብ ድጋፍ በአጠቃላይ 8,500,000 ብር መድረሱን ያሳያል ፡፡
በገንዘብ ድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የመቄዶንያ አምባሳደር ዲያቆን ሔኖክ ሀይሌ ለምዕመኑ ምስጋና ካቀረቡበኋላ አያይዘውም መቄዶንያ ከዋናው ማዕከል ውጪ በክልል ከተሞች አሁን ላይ ካለው 46 ቅርንጫፎች በተጨማሪ በየጊዜው አዳዲስ ቅርንጫፎችን እየከፈተ በየዕለቱ ጎዳና ላይ የወደቁና የተጎዱ ወገኖችን እያነሳ የሚገኝና ሁሌም እንደምለው ተቋሙ ለእኛ በየቀኑ የማንሳለመው ቤተክርስቲያናችን ነው ብለዋል፡፡
የባዝል ደ/ም/ ቅ /ሚካኤል ቤተክርስቲያንና ሌሎች ምዕመናን ያደረጉትን ድጋፍ ያስረከቡት ከሲውዘርላንድ የመጡት አባት ዛሬ እዚህ ተገኝተን በዓይኛችን ካየነው ድንቅ ሥራና ከተረጂዎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር የተደረገው ድጋፍ በውቅያኖስ ላይ አንድ ጠብታ እንደማፍሰስ ይቆጠራል ብለዋል ፡፡
የገንዘብ ድጋፉን የተቀበሉት የማዕከሉ መሥራችና ባለቤት ዶ/ር ብንያም በለጠ በበኩላቸው ለተጎዱ ወገኖቻቸው ከራሳቸው ቅድሚያ ሰጥተው በሲውዘርላንድ አብያተ ክርስቲያናን የሚገኙ ምዕመናን በጋራ በመሆን እስካሁን ድረስ ላደረጉት የ8.5 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ውጤታማ ሥራ ሰርተን እንጠብቃችኋለን ብለዋል::
