ሐና ጌራወርቅ
የሀዋሳ ከፍታ ወጣቶች ጥምረት፣ በከፍታ ፕሮጀክት ሥር በተለያዩ ከተሞች ከተዋቀሩ ጥምረቶች መካከል አንዱ ሲኾን፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እና በልዩ ልዩ የሕይወት መንገዶች ላይ የነበሩ ወጣቶችን በማሰባሰብ ለጋራ ዓላማ ተሰልፈው፣ ለመብታቸው በመቆም እና ድምፃቸውን በማሰማት፣ የሕብረተሰቡን ፍላጎት እውን ማድረግ ከቻሉ የወጣቶች ጥምረቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
በውጤቱም ይህ ‹‹የሀዋሳ ከፍታ ወጣቶች ጥምረት›› በሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ተወካዮቻቸውን በመላክ በጋራ ሊቋቋም ችሏል፡፡
ጥምረቱን በመመሥረቻ ጠቅላላ ጉባኤም የ24 ዓመቷ ሐና ጌራወርቅ፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በመመረጥ ለአንድ ዓመት ያህል ጥምረቱን ስትመራ ቆይታለች፡፡ እንደ እርሷ ገለጻ ወጣቶች በማኅበረሰባዊ የልማት ተግባራት ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳይኖራቸው የሚከለክሉ ሥር የሰደዱ ባሕላዊ እና ልማዳዊ አሉታዊ አመለካከቶች አሉ። በዚህም ሳቢያ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን በማዳበር፣ ለቤተሰባቸውም ኾነ ለማኅበረሰባቸው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማድረግ ሳይችሉ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ወጣቶች እንዲህ ካለ ተሳትፎ እንዲታቀቡ የሚደረጉት እንደ አቅመ ቢስ የሚቆጠሩ በመኾናቸው ነው፡፡ ይኽ የሚኾነው ወጣቶች የሕብረተሰቡ ሸክም እና አመጸኞች ተደርገው ስለሚታሰቡ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ደግሞ፣ ወጣቶች በጋራ ድምጻቸውን ለማሰማት የሚገናኙበት፣ የማኅበረሰቡን የቆዩ ደንቦች የሚቃወሙበት እና ዐቅማቸውን/ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ቋሚ መድረኮች አለመኖራቸውም፣ አዎንታዊ ሚናቸውን ለማዳበር፣ እምቅ አቅማቸውን አውጥተው ለመጠቀም እና በተደራጀ መልኩ ለማሕበረሰብ ልማት አስተዋፅዖ እንዳያደርጉ ምክንያት ኾኖ ኖሯል።
እንግዲህ እንዲህ ያለ ሥር የሰደደ ሁኔታ በሰፈነበት ወቅት ነው፣ የከፍታ ፕሮጀክት ሀዋሳ ላይ ደርሶ ትኩረቱን በወጣቶች ላይ ያደረገ ሥራውን የጀመረው፡፡ በሒደትም ቀደም ብለን የጠቀስነው የሀዋሳ ከፍታ ወጣቶች ጥምረት የተለያዩ ፍላጎቶች ካሏቸው ቡድኖች በተውጣጡ ቡድኖች በይፋ ተቋቁሞ፣ ወጣቶችን የሚያስተሳስር መደበኛ መዋቅር ከዘረጋ በኋላ ነው ሐና ጌራወርቅም በአመራርነት መመረጧን የምታስረዳው።
እንደ ሐና ገለጻ፣ ይኽ የተመሠረተው የከፍታ ለወጣቶች ጥምረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና ሌሎችም ተባባሪ አባላት በሕይወት ክህሎት፣ በማማከር፣ በንቁ የዜግነትና የሲቪክ ተሳትፎ፣ በተደራጀ አስተዳደርና አመራር፣ በገንዘብ አሰባሰብ፣ በማህበረሰብ ንቅናቄና በመሳሰሉት ልዩ ልዩ ዘርፎች የወጣቶች አቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን ሰጥተዋል፡፡ እነኚህ ሥልጠናዎችም ወጣቶችን በራስ በቅነት እና በመሪነት ብቃት ረገድ የነበራቸውን ክህሎት አሻሽሏል፡፡ እነዚህ የተለያዩ የዐቅም ማጎልበቻ የሥልጠና ፓኬጆች ደግሞ የጥምረቱ አባላትን ብቻ ሳይኾን፣ እርሷንም ጭምር የግል ሕይወቷን ከመቀየር አንስቶ፣ ጥምረቱ በማኅበረሰብ አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፍ አስችሎታል ስትል ሐና ትናገራለች።
የወጣቶች ጥምረቱ በዚህ ማኅበረሰባዊ ተሳትፎው፣ ‹‹ገበያ ዳር›› ተብሎ የሚጠራ አንድ ትምህርት ቤት ያለበትን ሁኔታ በመገምገም፣ ት/ቤቱ ከከፍተኛ የአካባቢ ጽዳትና ንፅሕና ችግር አንስቶ፣ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና በመጸዳጃ ቤት ንፅህና ጉድለት ምክንያት አብዛኛው የትምህርት ቤት አካባቢ ለወባ ትንኝ መራቢያ ሆኖ እያገለገለ በመኾኑ፣ በመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ ትልቅ ችግር እንደተፈጠረ፣ በተለይም ተማሪዎች በዚህ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መቅረት እና ማቋረጥ ውስጥ መግባታቸውን መረዳት ቻለ፡፡
የወጣቶች ጥምረቱ እንዲህ ያለውን ችግር ገምግሞ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ የት/ቤቱን ሁኔታ ለማሻሻል እና ለመማር ማስተማር ሥራውም ተስማሚ ይኾን ዘንድ ማኅበረሰብ ተኮር የኾነ ተግባራዊ የመፍትሔ ፕሮፖዛል አዘጋጀ፡፡ ፕሮፖዛሉ የአካባቢውን ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ ሥርዓትን በማሻሻል የት/ቤቱን ቅጥር ግቢና የመማሪያ ክፍሎችን ማስዋብን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ እናም ከተለያዩ ቡድኖች የተውጣጡ የትምህርቱ ቤት እና የአካባቢ ማኅበረሰብ አካላት ጋር ኾነው የተዘጋጀው ፕሮፖዛል በጀት ተመድቦለትና ዕውቅና አግኝቶ ተግባራዊ ሊኾን ችሏል፡፡
በተጨባጭም ይኸው የት/ቤቱን አጠቃላይ ንፅሕና ለማሻሻል ተግባራዊ የተደረገው ሥራ በትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ህይወት ላይ እጅግ አስደናቂ የሆነ ለውጥ አምጥቷል። በዚህ የተነሣም ሕብረተሰቡ በወጣቶች የማድረግ ዐቅም ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት በማረምም ኾነ በማኅበረሰብ ልማት ውስጥ ያላቸውን ሚና በአዎንታዊ መልኩ በመቀየር ረገድ ይኽ የሀዋሳ ከፍታ ለወጣቶች ጥምረት ትልቅ ሥራ ሰርቷል፡፡ በዚህም ትልቅ ኩራት ይሰማዋል።
ሐና ጌራወርቅም ወጣቱን እንዲህ ወዳለ ትስስር እና የጋራ መድረክ በማምጣት፣ ዐቅማቸውን ለማጎልበት እና ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ያሉ ማኅበራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጉ ከፍታ ፕሮጀክትን ታመሠግናለች። የመሠረቱት የወጣቶች ጥምረትም አባላቱን ለማሳደግ፣ በማኅበረሰብ ልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ለመሳተፍ፣ በሕብረተሰቡ እና በመንግሥት አካላት ውስጥ ያሉ ዳሩ ግን የተዛባ አመለካከት ያላቸውን ግለሰቦች አመለካከት ለመቀየር እና የወጣቶችን በተግባር የመፈጸም እምቅ ዐቅም ተጨባጭ በኾኑ ተግባራዊ ማሳያዎች ማሳመን እና ማሳደግ እንደሚፈልጉ ትገልጻለች።