አርባ ምንጭና አካባቢው በጣፋጭ የሙዝ ምርቱ ይታወቃል፡፡
ይህ የሙዝ ምርት ጥቅም ላይ ሲውል የቆየው ግን ከበሰለ በኃላ ተልጦ ለምግብነት በመጠቀም ብቻ እንደሆነ እናስታውሳለን፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥናት የተገኘ ሳይንሳዊ እውቀትን በመጠቀም ምርቱን በዱቄት መልክ አዘጋጅቶ ለምግብነት ማዋል መቻሉን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተክሉ ወጋየሁ ለጋሞ ቴሌቪዥን እንዳስታወቁት ሙዝን በዱቄት መልክ አዘጋጅቶ ለምግብነት ማቅብ የተቻለው በዩኒቨርሲቲው በሁለተኛ ዲግሪ በተደረገ ጥናታዊ ጽሁፍን ግኝት መሰረት ነው፡፡
ግኝቱ በሙዝ ምርት ላይ የሚከሰተውን ከፍተኛ ብክነት ማስቀረት ያስችላል ይላሉ፡፡
በተለይ, በህገወጥ ደላሎች ምክንያት የአካባቢው አርሶ አደሮች ከምርቱ ተገቢውን ጥቅም ሳያገኙ የሚቀሩበትን አካሄድ በማስቀረት ፋዳው የጎላ መሆኑን ነው ዶክተር ተክሉ የሚናገሩት፡፡
ሙዝን በዱቄት መልክ እያመረተ ለገበያ እያቀረበ የሚገኘው የአንጆ ኑስ ፕሮሰሲንግ መስራች አባል አቶ ጆን ከድር ድርጅቱ በሳምንት ከ10 ኩንታል በላይ የሙዝ ምርት ዱቄት እያመረተ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምርቱ እስከ ስድስት ወር ሳይበላሽ እንደሚቆይ ይናገራሉ፡፡
በገንፎ፣ ዳቦ፣ እንጀራ እና በሌሎችም የምግብ አይነቶ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ገልጸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለድርጅቱ ስኬት ያደረገው ድጋፍ ላቅ ያለ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የሙዝ ምርት በአዲስ መልክ ለምግብነት እየዋለ የሚገኝበት መንገድ በዩኒቨርሲቲዎች ጥናት እና ምርምሮች ሼልፍ ላይ ከመቀመጥ ወደ ተግባር መቀየር መጀመራቸው በተጨባጭ የሚሳይ ነው ይላሉ አቶ ጆን፡፡
በድርጅቱ የስራ እድል ከማግኘቷ በተጨማሪ በስራ መለወጥ እንደሚቻል ግንዛቤ እንደፈጠረላት ወጣት መራዊት አጥናፉ ትናገራለች፡፡
ጋሞ ቴሌቪዥን
