የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከየካቲት 1፣ 2018 ዓ፣ም ጀምሮ በመንግሥትና በግል ተሽከርካሪዎች ላይ ሐይማኖትን፣ ብሔረሰብን የጾታ ጥላቻን የሚያንጸባርቁ መልዕክቶችን መለጠፍ የሚከለክል ሕግ አወጣ።
የክልሉ ፖሊስ፣ በማናቸውም ተሽከርካሪ ላይ የሐይማኖት፣ የብሔረሰብ ወይም የጾታ ጥላቻን የሚያፀባርቁ ጽሑፎችን መለጠፍ፣ ጥቁር ስቲከሮችንና መስታወቶችን አስገጥሞ ማሽከርከር፣ ከነዳጅ ማደያዎች ውጪ ነዳጅ መቅዳት እና ትርፍ ወንበሮችን በተሽከርካሪዎች ላይ መግጠም በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አስታውቋል።
ሰሌዳ ፈተትቶ ወይም ያለ ሰሌዳ ማሽከርከር፣ መጋረጃ ጋርዶ ወይሞ አንጠልጥሎ ማሽከርከር፣ ከፍተኛ የሙዚቃ ድምጽ ማሰማት፣ ከፋብሪካ ተሽከርካሪዎች ውጪ የአደጋ ጊዜ መብራቶችን መግጠም፣ ደብዛዛ ወይም የተለያየ ቀለም ያላቸውን አዋኪ መብራቶች ገጥሞ ማሽከርከርም በክልከላው ውስጥ ተካተዋል።
የክልከላው ዓላማ የትራንስፖርት ደኅንነትን አስተማማኝ ማድረግና የወንጀል ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ክስተቶች መቀነስ እንደሆነ የጠቀሠው የክልሉ ፖሊስ፣ ከየካቲት 1 ጀምሮ ክልከላውን ተግባራዊ በማያደርጉ የመንግሥትም ሆነ የግል አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
