የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም በ2018 በጀት ዓመት በ6 ወራት ውስጥ በዕቅድ ከያዛቸው ተግባራት መካከል በ20 ጉዳዮች እና በ46 ተቋማት ላይ ቁጥጥር አድርጎል።
በተደረገው ቁጥጥር በተለዩት በ 100 የአሰራር ክፍተቶች ላይ ስምምነት የተደረሰባቸው ግኝቶች ናቸው፡፡ በዚህም አንደኛው በፌዴራልና በተመረጡ ክልሎች በማዕድን ዘርፍ ላይ ፈቃድ መስጠት፣ ማደስ እና ማገድ ጋር በተያያዘ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የተከናወነ ቁጥጥር መሆኑን የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አንለይ ወርቄ ተናግረዋል።
በዚህም ከተለዩ ክፍተቶች መካከል በአንዳንድ ክልሎች በማዕድን ዘርፉ ፈቃድ አሰጣጥ አንጻር ከተሰጣቸው ስልጣንና ተግባር ውጪ ፈቃድ የሚሰጡበት ሁኔታ መኖሩና ይህንንም ለመግታት በፌዴራል በኩል የተሰራው ስራ በቂ አለመሆኑ ተጠቁሟል።
በተለይም በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በብረት ማዕድን፣ ሌላው በአንዳንድ ክልሎች ከፌዴራሉ አዋጅ በሚጻረር መንገድ የራሳቸውን አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ የሚያወጡበት አካሄድ መኖሩ ተነግሯል፡፡
ሁለተኛው በፌዴራልና በተመረጡ ክልሎች በሲቪል ሰርቪስ መ/ቤቶች የመንግስት ሰራተኞች ከህግ ውጭ የሚፈጸሙ፣ ቅጥር፣ ደረጃ ዕድገት፣ ዝውውር እና የደመወዝ መቆረጥ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎች መሆናቸው ተገልጿል።
በዚህም የሰራተኞች የወር ደመወዛቸው በወቅቱ አለመከፈሉና በፐርሰንት እንደሚከፈል ቀሪ ክፍያቸው ደግሞ አሁንም ድረስ በተለያዩ ክልሎች፣ በአንዳንድ ዞኖች እና ወረዳዎች ያልተከፈላቸው ሰራተኞች ላይ የአስተዳር በደል እየተፈፀመ ነው።
አክለውም የመንግስት ሰራተኞች ለተለያዩ የልማት ስራዎች በሚል የኤችአይ ቪ፣ የልማት ማህበር በሚል ያለ ሰራተኛ ፈቃድ እየተቆረጠባቸው መሆኑ ከህግ አግባብ ውጪ በአንድ የስራ መደብ መታወቂያ ቁጥር ከአንድ በላይ ቅጥር እየተፈፀመ መሆኑ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አንለይ ወርቄ ጨምረው ተናግረዋል።
ብስራት ሬዲዮ
