በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የረድኤት ተቋማት እና በሰላም ላይ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሥራዎቻቸው ግጭትን ያገናዘበ እና ችግር የማይፈጥር መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው ሲል፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የግብረ ሰናይ ተቋማትን የያዘው “Ethiopia Conflict sensitivity Hub” ገልጿል።
የማዕከሉ ዳይሬክተር ሞገስ ሽፋራው (ዶ/ር) የረድኤት ተቋማት እና በሰላም ላይ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በጎ አላማን መሰረት አድርገው ሲነሱ፤ በሌላ ወገን የሚሰሩት ሥራ ሌላ ችግር ወይንም ግጭት ሊያመጣ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ገልጸዋል።
ለዚህም የሚደረጉ ድጋፎች ለተገቢው አካል አለመድረስ፣ የተወሰነ ክፍልን ያገለለ መሆንና ሌሎችም ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ስለሆነም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚሰሯቸው ሥራዎች እነዚህን ከግምት ያስገቡ መሆን አለባቸው ብለዋል።
ማዕከሉ ከተቋቋመ ስድስት ወራትን ማስቆጠሩንና በዚህ በሰብዓዊ እርዳታ አሰጣጥ ሂደት የሚፈጠሩ ለማስቀረት የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
“ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል አንደኛው ጥናት ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ “ድጋፍን ለማድረግ ወደስፍራው ከማቅናት በፊት ሀገር ውስጥ ያለው ወይም የነበረው ግጭት ምን አይነት ነው?፣ ሚዛኑ ምን ይመስላል? እንዲሁም ምን ችግር ይዞ ይመጣል? የሚለው ይጠናል” ብለዋል።
ይህም ማስተካከያዎችን በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል። ግጭትን ያገናዘበ ሥራ (Conflict sensitivity) በኢትዮጵያ አዲስ ሀሳብ መሆኑን ገልጸው፤ ሥራውን ለመስራት አቅም የሚፈልግ በመሆኑ አቅም የማጎልበት ሥራ ይሰራል ብለዋል።
እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት የራሳቸው የሆነ ስትራቴጂ እና ፓሊሲ ያላቸው ሲሆን፤ አንድ ላይ መጥተው የጋራ የሆነ ደረጃ እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሐዱ ራዲዮ
