ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ህዳር 12 ቀን ሲከናወን የቆየው አከባቢን በማጽዳት ቆሻሻን የማቃጠል ስርዓት አሁን ላይ የተከለከለ ድርጊት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
በያዝነው ህዳር ወር በመዲናዋ በየትኛውም አከባቢ ህዳር ሲታጠን በሚል ቆሻሻን ሰብስቦ ማቃጠል በሕጉ መሰረት የሚያስቀጣ መሆኑን የገለጹት በአዲስ አበባ ከተማ የአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአከባቢ ብክለት ክትትል እና ቁጥጥር ዘርፍ ቡድን መሪ ወይዘሮ ሰናይት ተስፋዬ ናቸው፡፡
ይህንን ለማስፈጸም የደምብ ማስከበር ባለስልጣን ባለሙያዎችን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ህዳር ሲታጠን የሚለውን ስርዓት በተሻለ መንገድ መተግበር ይገባል የሚሉት የዘርፉ ቡድን መሪዋ፣ በእለቱ የአዲስ አበባ ጽዳት አገልግሎት በሁሉም አከባቢዎች ቆሻሻ የመሰብሰብ መርሃ ግብር እንደሚያከናውን አስታውቀዋል።
ቡድን መሪዋ ማንኛውም ግለሰብ ቆሻሻ በማቃጠል አከባቢውን ብሎም መዲናዋን ከሚበክል ድርጊት መቆጠብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ከያዝነው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ መቆየቱን እና እስከ ህዳር 12 ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
[መነኻሪያ ሬዲዮ]
