የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ወደ ሶማሊላንድ በረራ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችን፣ በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ፍላይዱባይን፣ የገንዘብ ቅጣት እና ከሶማሊያ የአየር ክልል የመታገድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ይህ የሆነው አየር መንገዶቹ ሞቃዲሾ አስገዳጅ ያደረገችውን የኢ-ቪዛ መስፈርት ችላ በማለት ተሳፋሪዎችን ወደ ሶማሊላንድ ማጓጓዛቸውን ተከትሎ ነው።
የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንዳስታወቀው፣ ኤሚሬትስ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ፍላይዱባይ በሞቃዲሾ የኦንላይን ሥርዓት የሚሰጠውን ኢ-ቪዛ ያላገኙ ተሳፋሪዎችን ወደ ሶማሊላንድ አውሮፕላን ማረፊያዎች ማጓጓዙን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ደርሰውታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀደም ሲል የፌዴራሉን የኢ-ቪዛ መስፈርት ትቶ፣ በሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ትዕዛዝ መሰረት ተሳፋሪዎች በሃርጌሳ ኢጋል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ቪዛ እንዲያገኙ የሚያስችለውን ሥርዓት መከተሉ ተጠቅሷል።
ፍላይዱባይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመቀላቀል ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥትን ሥልጣን በቀጥታ የሚገዳደር ሆኗል ተብሏል።
የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ትዕዛዙን የማያከብሩ አየር መንገዶች የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው እና ከሶማሊያ የአየር ክልልና አውሮፕላን ማረፊያዎች ሊታገዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
በምላሹ፣ የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት እኤአ ኖቬምበር 10 ቀን 2025 ጀምሮ ወደ ክልሏ የአየር ክልል ለሚገቡ ዓለም አቀፍ በረራዎች ሁሉ የቅድሚያ የበረራ ፈቃድ እንዲያገኙ ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል።
capital news
