የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 11ኛው ዓመታዊ የፎርብስ ሴት የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ የዕድሜ ዘመን ትጋት ሽልማትን አግኝተዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በመሆን ለስድስ ዓመት ያገለገሉት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ፣ በተለያዩ አገሮች በአምባሳደርነት እንዲሁም በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርተዋል::
በፈረንሣይ ሞንተፔለ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ምሩቋ፣ እ.ኤ.አ. ከ1989 እስከ 1993 ተቀማጭነታቸውን ሴነጋል በማድረግ የማሊ፣ የኬፕ ቨርድ፣ የጊኒ ቢሳዎ፣ የጋምቢያና የጊነ አምባሳደር፣ እ.ኤ.አ 1993 እስከ 2002 በጅቡቲ አምባሳደርና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ቋሚ ተወካይ፣ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል፣ እ.ኤ.አ. በ2011 በኬንያ የተባበሩት መንግሥታት ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ማገልገላቸው በከፍተኛ ኃላፊነት ከሠሩባቸው ሥራዎች ይጠቀሳሉ::
ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት አፍሪካውያን መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና ምሁራን ከተገኙበት ጉባዔ ጎን ለጎን ከፎርብስ አፍሪካ ዋና አዘጋጅ ጎድፍሬይ ሙቲዝዎ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በማኅበረሰብ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሴቶች ወደ አመራርነት መምጣት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል::
ስለሴቶች መብት መከበርና ስለ ሰላም አስፈላጊነት ባገኙት መድረክ በመናገር የሚታወቁት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ፣ ሴቶች መር የሆነ የማኅበራዊ ለውጥ አስፈላጊነትና ሴቶች የመምራት ሚናን መያዝ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል:: በጉባዔውም አንዱ አጀንዳ ለነበረው ‹‹በአፍሪካ የሴቶች የኢኮኖሚ ተሳትፎ እንደ ሕጋዊ መሥፈርት እንዲወሰድ›› ለሚለው ውይይት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል::
‹‹እንዲህ ዓይነቱ መሥፈርት የፆታ አሳታፊነት ተግባራዊ እንዲሆን የተወሰነ ዋስትና ይሰጣል በማለት:: የፆታ እኩልነትም ምኞት ይሰጣል፤›› ብቻ ሳይሆን እውነታ እንዳለበትም ጠቁመዋል::
ከሪፓርተር
