ሪች ፎር ቼንጅ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የትምህርት ስርአትን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚሰሩ 12 አዳዲስ በትምህርት-ቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪዎችን መርጦ ወደ ስራ ማስገቡን አስታወቀ።
ድርጅቱ ላለፉት አስር አመታት ማህበራዊ ስራ ፈጣሪዎችን ሲደግፍ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው መርሃ-ግብር መሰረት እነዚህ 12 አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎች ቀደም ሲል ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩትን 24 ተቀላቅለዋል። ይህም በአጠቃላይ በዘርፉ ድጋፍ የሚያገኙ ስራ ፈጣሪዎችን ቁጥር ወደ 36 አድርሶታል።
የሪች ፎር ቼንጅ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት መቅድም ጉልላት እንደገለጹት፣ የተመረጡት ስራ ፈጣሪዎች የሀገሪቱን የትምህርት ካሪኩለም እና የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ያገናዘቡ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን የሚያቀርቡ ናቸው።
ለእያንዳንዱ ስራ ፈጣሪ ድርጅት እስከ 60 ሺህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፣ ከገንዘቡ በተጨማሪም የቢዝነስ ክህሎት ስልጠና፣ የኮቺንግ አገልግሎት እና ከአሜሪካው ካርኒጊ ሜለን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቴክኒክ እገዛ እንደሚደረግላቸው ተገልጿል።
ይህ የአምስት አመት ፕሮጀክት በዋነኝነት ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ያሉባቸውን የፋይናንስ እና የክህሎት ክፍተቶች በመሙላት፣ የፈጠራ ስራዎቻቸው ወደ ሰፊ ገበያ እንዲወጡና በትምህርት ተደራሽነት ላይ ለውጥ እንዲያመጡ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
