የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያደረጉት ተደጋጋሚ ንግግር የአሜሪካንን የዳበረ የዲፕሎማሲ ባሕል የማይመጥን ነው

Date:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሜሪካ የገንዘብ እርዳታ እንደተሰራ በመግለጽ ያደረጉትን ንግግር እንደማይቀበለው አስታውቋል።

ኢዜማ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ማንኛውም አካል ለሕዳሴው ግድብ የሞራል፣ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ ድጋፍ አድርጎም ቢሆን፤ ኢትዮጵያውያን ግድቡን ለመፈፀም ያደረጉትን ያህል እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ተጋድሎ በሚመጥን ደረጃ ያደረገ እንደሌለ ገልጿል።

“እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በተደጋጋሚ እና በአደባባይ ግድቡ በአሜሪካ ገንዘብ እንደተገነባ የሚገልጽ የስህተት ንግግር ማድረጋቸው ስህተት ነው” ብሏል።

የፕሬዝዳንቱ ንግግር ኢትዮጵያ መሥራች አባል በሆነችበት የተባበሩት መንግሥታት ኮንቬንሽን አንቀጽ 2  ቁጥር አንድ የተደነገገውን የሁሉንም አባል ሀገራት ሉዓላዊ እኩልነት ድንጋጌ የሚፃረር እና የአሜሪካንን የዳበረ የዲፕሎማሲ ባሕል የማይመጥን መሆኑንም አመላክቷል።

ከአሜሪካ በተጨማሪም “አንዳንድ የግብጽ ባለሥልጣናት ይህንኑ የፕሬዝዳንቱን አድሏዊ ንግግር እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የሕዳሴው ግድብ ላይ በአዲስ መልክ የጀመሩት አፍራሽ ቅስቀሳ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶቿ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን የሚክድ ብቻ ሳይሆን በመልካም ጉርብትና አብሮ የመልማት እድሎችን የሚያጨልም እንዳይሆን ቆም ብለው እንዲያስቡ እናሳስባለን” ብሏል።

ከመርሆዎቹ ቀዳሚው የኢትዮጵያ እና የሕዝቦቿ ጥቅም ምንጊዜም ቅድሚያ እንደሚኖረው ስለመሆኑ የገለጸው ፓርቲው፤ የኢትዮጵያውያን ጥቅምና ኩራት ማሳያ የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች በዝተው ማየት እንደሚፈልግ አስታውቋል።

“ድህነትና ጉስቁልናን ለመጫው ትውልድ ማውረስ የለብንም፣ ብሔራዊ ሀብታችንን ለዜጎች ጥቅምና ክብር መልማት አለባቸው ብለን፤ በቆራጥነት ወጥነን ከዳር ካደረስናቸው ፕሮጀክቶች ዋነኛው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደሆነ ይታወቃል” ሲልም በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ኢዜማ አክሎም፤ “የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያለን የፖለቲካ ኃይሎች፣ ምሁራን፣ የማኅበረሰብ መሪዎች እና አንቂዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና መላው ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ከጊዜያዊ ልዩነቶቻችን ይልቅ ዘላቂ የሆነ ብሔራዊ ጥቅማችንን፣ ክብራችንን እና የልጆቻችንን መጻኢ እድል በማሰብ ይህንን ዐይን ያወጣ አድሎአዊነት የማንቀበለው ብቻ ሳይሆን በጋራ የምናወግዘው እና የምንመክተው መሆኑን ሁሉም እንዲያውቀው በጋራ እንድንቆም ጥሪ እናቀርባለን” ሲል ገልጿል።

“በድህነታችን ሊከብሩ፤ ባለመተባበራችን የእርዳታቸው ደጅ ጠኚ እና ለማኝ ሊያደርጉን ለሚፈልጉ ሁሉ መልዕክታችን አንድ መሆን አለበት” ሲልም አሳስቧል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ውጭ ምንዛሪ የሚያድኑ የሴራሚክ ምርቶች በቅርቡ ለገበያ ይቀርባሉ

ይህ የተገለፀው ኢትዮደር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ”Golden Tier...

የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተገለጠ

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና አቅርቦት ላይ ተፈጥሮ የነበረው ስጋት...

አሜሪካ የኢራንን የጭነት መርከብን መያዟን አስታወቀች

በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የዘጋችው...