የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (IRGC) ከፍተኛ አዛዥ፤ አገሪቱ ሚሳይል እና ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የማስወንጨፊያ መሠረተ ልማቶቿን አሁን ባለው የተኩስ አቁም ወቅትም ጭምር ከጦርነቱ በፊት ከነበረው በበለጠ ፍጥነት እያደራጀች መሆኑን ገለጹ።
ኑር ኒውስን ዋቢ አድርጎ አልጀዚራ እንደዘገበው፤ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የኤሮስፔስ ክፍል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ማጂድ ሙሳቪ የኢራን የማስወንጨፊያ ስርዓቶች መልሶ ግንባታ እና የማዘመን ሂደት መፋጠኑን ተናግረዋል።
ጄኔራል ሙሳቪ ከመሬት በታች የሚገኝ የሚሳይል ተቋምን በሚጎበኙበት ወቅት በሰጡት አስተያየት፤ “በተኩስ አቁም ወቅት የሚሳይል እና የድሮን ማስወንጨፊያዎችን የማዘመን እና የመተካት ፍጥነታችን ከጦርነቱ በፊት ከነበረውም የላቀ ነው” ብለዋል።
አዛዡ የኢራንን አቋም ከተቃዋሚዎቿ ጋር በማነፃፀር፤ “ባላንጣዎቻችን የጦር መሣሪያ ክምችታቸውን እንደ እኛ በፍጥነት መልሰው መገንባት አልቻሉም” ያሉ ሲሆን፣ ባላንጣዎቻቸው አሁንም በውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሙሳቪ አክለውም ኢራን እና አጋሮቿ በግጭቱ የበላይነት ማግኘታቸውን፤ በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ፣ በሊባኖስ እና በአጠቃላይ በቀጠናው ያለውን ሁኔታ በማንሳት “በዚህኛው የጦርነት ምዕራፍ ተሸንፈዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
