አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል
(የ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› መጽሐፍ ደራሲ)
ግዮን መጽሔት :- አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስመረቁት ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› የሚለው መጽሐፋቸው በብዙ የሕግ፣ የታሪክና የፖለቲካ ሰዎች ዘንድ አነጋጋሪ መጽሐፍ ኾኗል፡፡ ፀሐፊው ፍሬሕይወት ሳሙኤል የቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኾነው ከመሥራት አንስቶ፣ በአይረሴው ምርጫ 97 ወቅት በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙርያ በወቅቱ ኸነቱን አንዲያጣራ በፖርላማ የተቋቋመዉ ኮምሽን በሰብሳቢነት መርተው ሀገርና ፍትሕ የጣለችባቸውን አደራ በሚገባ የተወጡ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡
ሙያቸውን በተግባር የተፈተኑ ተሞክሯቸውን መሠረት አድርገው የጻፉት መጽሐፋቸው በብዙዎች ዘንድ ትኩረት ሳቢ እንዲኾን ምክንያት ኾኗል፡፡ በመጽሐፉ ይዘቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር ያደረጉት ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፦ በቅርቡ ‹‹የሕገ መንግሥት ተቃርኖዎች›› የሚባል አዲስ መጽሐፍ አዘጋጅተሃል ፤ ለመፃፍ ምን አነሳሳህ?
ፍሬሕይወት:- በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ችግሮች መካከል ጥቂት የማይባሉት መነሻቸው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ችግሮቹ መዋቅራዊና ምክንያታዊ ናቸው፡፡ ሕገመንግሥቱ ደግሞ በርካታ ችግሮችን ሊፈታ የወጣና ብዙ ጥሩና ሊስተካከሉ የሚገባቸው ሀሳቦች ያሉት ነው፡፡ በሌላ በኩል ሕገ መንግሥቱ የሚነካው በመቃብራችን ላይ ነው የሚሉ አሉ፡፡
ሌሎች ደግሞ ቀዳደን እንጥላለን ይላሉ፡፡ ሁለቱም ኃይሎች የአንድ ሀገር ልጆች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱን ቀዶ መጣልም ሳያስፈልግ እሱን ለመከላከል መሞትም ሳያስፈልግ ሕገመንግሥቱ ምን ይላል የሚለውን አይተው የሚከራከሩበትንና የሚሻሻልበትን መንገድ ለመፈለግ አንድ ሰነድ ያስፈልጋል በሚል መነሻ ነው መጽሐፉን ለመፃፍ የተነሳሁት፡፡
ግዮን፦ መጽሐፉን ለማዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ ወሰደብህ?
ፍሬሕይወት፦ ወደ ሁለት ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ወስደብኛል፡፡
ግዮን፦ የመጽሐፉ ምርቃት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እሸቱ ጮሌ አዳራሽ ነበር የተካሄደው፤ የቦታ ምርጫው ከገጠመኞችህ ጋር የተገናኘ ነው?
ፍሬሕይወት:- የተለየ ገጠመኝ የለኝም፡፡ ትምህርቴን የጨረስኩት አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዬን የሕግ ትምህርት የተማርኩት እዚያው ነው፡፡ የመጽሐፉ ምረቃም እዚሁ ዩኒቨርሲቲ ይሻላል በሚል ነው ያደረግኩት፡፡ ምንም የተለየ ትርጉም የለውም፡፡ ይህን የመሰለ ጉዳይ ጽፌ ሌላ ቦታ የግል ተቋም ከሚመረቅ እዚያ ቢመረቅ ይሻላል ብዬ ነው ቦታውን የመረጥኩት፡፡
ግዮን፦ የመጽሐፉ ምርቃት ላይ በርካታ እንግዶች ተጋብዘው ነበር፤ በመጽሐፉ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተመረጡት ሰዎች እነማን ናቸው? መድረክ ላይ የቀረቡት ሰዎች የተለየ ምክንያት አላቸው?
ፍሬሕይወት:- ተጋባዥ እንግዶቹ ውስጥ በብዛት የሕግ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ከዚያ ውጭ ደግሞ የሕግ ባለሙያ ያልኾኑ ግን ደግሞ የተለየ እይታ ሊኖራቸው ይችላሉ ብለን የመረጥናቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ ከህወሓት ነባር ታጋዮች ውስጥ አቶ ገብሩ አሥራት አንዱ ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ ሕገ መንግሥት ሲወጣ ህወሓት ከነበረዉ ትልቅ ድርሻ አንፃር እሳቸውም በህወሓት ውስጥ ትልቅ ሚና የነበራቸው በመኾኑ ነው፡፡ ስለዚህ እዚያ ላይ እሳቸው የሚሉት ነገር በጣም አስፈላጊ ነበር፡፡
ሁለተኛው አንባቢ አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ የሚባሉ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ ጠበቃና የሕግ አስተማሪም ናቸው፡፡ ሌላው ሰው ደግሞ ዶ/ር ጆቱ ይባላሉ። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስቴር ዲኤታ ማዕረግ የሕግ አማካሪ ናቸው፡፡ ሌላው ክቡር አቶ ዘካሪያስ ኤርኮላ የሕግ ጥናትና ምርምር ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክቶሬት ናቸው፡፡ በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አባል ናቸው፡፡
አቶ ጋረደው አሰፋ ከግጭት አንፃር አስተያየት የሰጡ ናቸው፡፡ በስም ያልጠቀስኳቸው ብዙ ታዋቂ ሰዎች ነበሩ አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡ ፕሮግራሙ ጥሩ ነበር፡፡ ሕገመንግሥት ደረቅ የሕግ ጉዳይ ብቻ ሳይኾን አጠቃላይ የፖለቲካና ማሕበራዊ ጉዳዮች መቋጠሪያ መሠረት ስለኾነ የሕግ ባለሙያዎችም ባለሙያ ያልኾኑትም እንዲሳተፉ አድርገናል፡፡
ግዮን፦ መጽሐፉ ወደ ሕትመትም ወደ ገበያም ከመግባቱ በፊት አይተው ሀሳብ አስተያየት እንዲሰጡ የተጋበዙ ሰዎች ነበሩ? አስተያየታቸውስ ገንቢ ኾኖ የጠቀመህ አለ ወይ?
ፍሬሕይወት:- የመጽሐፉ የምስጋና ክፍል ላይ ብዙ ሰዎች ጠቅሻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ኃላፊነት ውስጥ ያሉ ሰዎች፤ በውጭ በተለያዩ ዩንቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ ፕሮፌሰሮች እንዲሁም ስለኢትዮጵያ ብዙ ያነበቡና የተመራመሩ ብዙ የፃፉም ሰዎች አስተያየት ሰጥተውኛል፡፡ ሁሉም ገንቢ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ፖለቲካዊ ጭቅጭቅ ከተነሳ በሚል በምስጋናው ክፍል ያላካተትኳቸው አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሴንሴቲቭ ነገሮችን ስለሚያነሳ በመጽሐፉ ዙሪያ አላስፈላጊ ውዝግብ ከተነሳ የሰዎቹ ስም እዚያ መኖር ስለማይጠቅም ቀርቷል፡፡ ነገር ግን በጣም በርካታ የሥነ ልቦና፧ የታሪክ የሕግና መሰል ዘርፎች ምሁራን ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ግዮን፦ የመጽሐፉን ርዕስ ‹‹የሕገ መንግሥት ተቃርኖዎች›› ያልከው ከምን አንጻር ነው?
ፍሬሕይወት:- በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ተቃርኖዎች አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ሐሳብ በቀረበባቸው አንቀጾች ላይ ተመሳሳይ አቋም የለም፡፡ ሁሉም ይሻሻል የሚሉ አካላት የተለያየ አቋም ያላቸው ናቸው፡፡ አንዱ የመጽሐፉን ርዕስ በተቃርኖ እንድሰይም ያደረገኝ ይኼ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሕገመንግሥቱ የሚለውና መሬት ላይ ያለው ሐቅ የተቃረነ መኾኑ ነው፡፡
ለምሳሌ ሕገመንግሥቱ መገንጠልን ይፈቅዳል የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ኢትዮጵያ እንድትገነጣጠል ሳይኾን እንድትቀጥል ብዙ ዋጋ ይከፍላል፡፡ በሀገራችን ከፍተኛ የደም ዋጋ የሚከፈለው ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ በራሱ ተቃርኖ ነዉ፡፡ እያንዳንዱ ሀሳብ ውስጥ ተቃርኖ አለ፡፡ ሕመንግሥቱን በተመለከተ ወጥ የኾነ አተያይ የለም፡፡ ለምሳሌ የክልሎችን አወቃቀር አንዱ ሸጋ ነው ሲል ሌላው ደግሞ በፍጹም አያስኬድም ይላል፡፡ አንዱ አንቀጽ 39 ጥሩ ነው ሲል ሌላው ደግሞ አያስኬድም ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱም መሬት ላይ ካለው የሕዝቡ እምነት ጋር ተቃርኖ አለው፡፡ እነዚህን ነገሮች ከግምት በማስገባት የመጽሐፉ ርዕስ ይህ ሊኾን ችሏል፡፡
ግዮን፦ መጽሐፉ ብዙ የተደከመበትና እንደሀገር ይጠቅማል ተብሎ የተሰናዳ ከመኾኑ አንፃር በመንግሥት እንደ ግብዓት የሚወስደው ይመስልሃል? በዚህ ዙሪያ ተስፋ የምታደርገው ምንድነው?
ፍሬሕይወት:- መንግሥት ይጠቀምበታል ብዬ አስባለሁ። መንግሥት ማለት ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ ነው፡፡ መንግሥት ከሕዝብ ማኅፀን የወጣ ነው፡፡ ሕዝብ እስከወደደው ድረስ መንግሥትም ይወደዋል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ያነበቡ የመንግሥት ሰዎች ሁሉ ይህ መጽሐፍ ለሕገ መንግሥት ማሻሻያው ጥሩ ግብዓት ነው ብለው ተቀብለውታል፡፡ አስተያየት ከሰጡ ሰዎችም ለምሳሌ ሁሉም የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን መጽሐፉ ደርሷቸው ስለመጽሐፉ ጠቀሜታ በከፍተኛ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
ስለዚህ መጽሐፉ በመንግሥት በኩልም ይሁን በተቃዋሚው ወገን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ መጽሐፉን አንብበው ሚዛናዊ ሀሳብ የሰጡ የመድረክ አቅራቢዎች እንዳሉትም ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በምርቃቱ ወቅት የተለያዩ የመከራከሪያ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡ ሚዛናዊ ሀሳቦች ቀርበውም ሁሉም ተቀብሎታል፡፡
ግዮን፦ በመጽሐፉ ምርቃት ዕለት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ሁሉም የኮሚሽኑ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ የተጋበዙበት የተለየ ምክንያት አለ?
ፍሬሕይወት፦ በእርግጥ ጥሪው በሀገር ደረጃ ሲኾን በርካታ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎችንም የጨመረ ነበር፡፡ አማራጭ የፖለቲካ ተቃዋሚ ኃይሎችም ተጋብዘዋል፡፡ አጋጣሚ ኾኖ የጠቀስካቸው ተቋም አመራሮች ሊገኙ ችለዋል፡፡ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሸነርና ምክትላቸውም ተገኝተዋል፡፡ ይህ የኾነው ጉዳዩ የሚመለከታቸው በመኾኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሌሎች የመንግሥት አካላት ያልተገኙት በምርቃቱ ዕለት ተደራቢ ስብሰባ ስለነበር ነው፡፡ የኾኖ ኾኖ የምክክር ኮሚሽኑ በሀገር ደረጀ ተግዳሮት የኾኑ ሕገመንግሥት ወለድ ስጋትና የግጭት ምንጮችን አቅልሎ በማምጣት በምክክር ለመፍታት እየሠራ የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ ለእነሱ ትልቅ ግብዓት ነው፡፡
ብዙዎች እንደውም ከዚህ አንፃር ሰነድ አዘጋጅቶ ሰጣቸው እያሉ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አንዱና ዋናው ችግር ሕገ መንግሥቱ ስለኾነ ይህን ችግር በዋናነት እያተከታተሉ ያሉት ደግሞ እነርሱ በመኾናቸው የእነርሱ መገኘት ትክክለኛና አግባብ ያለው ነበር፡፡ እነርሱም መጽሐፉን እንደአንድ ግብዓት እያዩት እንደኾነ ሰምተናል፡፡
ግዮን፦ መጽሐፉን ስታዘጋጅ እንደሀገር የተሻለ ሕገመንግሥት አላቸው ብለህ በተሞክሮ ደረጃ የወስድካቸው ሀገሮች አሉ? እንደ ማጣቀሻ የተጠቀምካቸው መሰል ሰነዶችስ አሉ?
ፍሬሕይወት:- መጽሐፉን ሳዘጋጅ በዋናነት መሠረት ያደረግኩት የእኛ ሕገመንግሥት ሲዘጋጅ ቃለጉባዔ የተያዘበትን ሰነድ ነው፡፡ እነዚህ ቃለ ጉባዔዎች ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛው ቃለ ጉባዔ የሕገመንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ነው፡፡ ሙሉ ቃለ ጉባኤው ነበረኝ፡፡ ሁለተኛው የሽግግር መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለዚህ ሕገመንግሥት የተነጋገረበት ቃለ ጉባዔ ነው፡፡
ይኼም አለኝ፡፡ ሦስተኛው በሀገር ደረጃ የሕገ መንግሥት ምርጫ ተደርጎ የተያዘን ቃለ ጉባኤን ተጠቅሜያለሁ፡፡ ይህም ቃለ ጉባኤው ነበረኝ፡፡ ስለዚህ በዋናነት የሌሎችን ሀገሮች ሀሳብ ከማጣቀስ ይሄ ሕገ መንግሥት ሲረቅ ተሰብሳቢዎች ምን ነበረ የሚሉት የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በወቅቱ የፖለቲካ ጉልበት የነበረው ብቸኛው ህወሓት ወይም ህወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ምን ሲልና ሲያደርግ ነበር፣ ተሳታፊዎቹስ ምን ሐሳብ ሲያነሱ ነበር? ተሳታፊዎቹስ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክሉ ነበሩ ወይ? የሚለውን ዝርዝር ነገር መነሻ ያደረግኩት የሌለውን ሀገር ሳይኾን የሀገራችንን ኢትዮጵያን ቃለ ጉባኤ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምን ስንል ነበረ ብለን መልሰን ራሳችንን ለዳኝነት ማቅረብ ጥሩ ነው፡፡ ራሳችንን ከማየት ብንነሳ ብዬ የራሳችንን ቃለ ጉባኤን ነው የተጠቀምኩት፡፡
ግዮን:- እንደ ኢትዮጵያ ላለ 130 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለሚኖርባት በርካታ የአመለካከት ብዝኃነትም ላለባት ሀገር ሕገ መንግሥት እንዴትና በነማን ነው መረቀቅ ያለበት? የሚሉትንና ተጨማሪ ጥያቄዎች በመያዝ በሚቀጥሉት ቀናት ሁለተኛዉን ክፍል ይዘን እንቀርባለን ።
