አሜሪካ 250ኛ ዓመት የጦር ሠራዊቷ የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከፍተኛ ወታደራዊ ትዕይንት በዋሽንግተን ዲሲ እያሳየች ትገኛለች።
‘ለረጅም ጊዜ ይህን ዝግጅት የማካሄድ ሕልም ነበራቸው’ የተባሉት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከ6 ሺህ በላይ ወታደሮች፣ 150 ተሽከርካሪዎች እና 50 የጦር አውሮፕላኖች የሚሳተፉበት ትዕይንት ላይ ተገኝተው እየተከታተሉ ነው።
በዛሬው ዕለት 79ኛ ዓመት ልደታቸውን እያከበሩ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሰልፉን አስመልክተው በትሩዝ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወታደራዊ ትዕይንቱ የአሜሪካ ወታደሮች በታላላቅ ታሪካዊ ድሎች የተጫወቱትን ሚና የሚዘክር እና የአሜሪካን አቅም የሚያሳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
እንደ ፈረንሳይ እና ሩስያ ያሉ ሀገራት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የድል ቀንን ለማስታወስ ተመሳሳይ ወታደራዊ ትዕይንቶችን የሚያካሄዱ ቢሆንም፤ አሜሪካ ግን የባሕረ ሰላጤውን ጦርነት ማብቃት አስመልክቶ 8 ሺህ ወታደሮች የተሳተፉበትን ወታደራዊ ትዕይንት ያካሄደችው ከ34 ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1991 ነበር።
45 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለው ይህ ትዕይንት የፕሬዚዳንቱን አባካኝነት ያሳብቃል በሚል ትችት እየቀረበበት ይገኛል።
ወታደራዊ ትዕይንቱን የተቹት ዲሞክራቶች ለዚህ ዝግጅት የሚወጣው ገንዘብ ለወታደር ቤተሰቦች ቢውል የተሻለ ነበር የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።
ጉዳዩን አስመልክተው ለኤንቢሲ ሀሳባቸውን የሰጡት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ለዚህ የሚወጣው ወጪ ከዓላማው እና ውጤቱ ጋር ሲነጻጸር ኢምንት ነው ብለዋል።
“በዓለም ላይ ታላላቅ ሚሳኤሎች፣ ታላላቅ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች፣ ታላላቅ የጦር ታንኮች፣ በአጠቃላይ ታላላቅ የጦር መሣሪያዎች አሉን፤ እናም ይህን ማሳየት እንፈልጋል” በማለት ነው ፕሬዚዳንቱ ለምን ወታደራዊ ትዕይንቱ እንዳስፈለገ የገለጹት።
