የአገው ፈረስ ባህልን በዩኔስኮ የማይዳሰስ የሰው ልጆች ወካይ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ የተዘጋጀው በአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ እና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አማካኝነት ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋየ እንደገለጹት፤ “በጥር ወር አገው ምድር ይለያል፤ የአገው ፈረስ በምድር እንደ ንስር” እንደሚባለው ሁሉ፣ የአገው ሕዝብ ይህ ታላቅ እሴቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝና በቅርስነት እንዲመዘገብ ለዘመናት ሲጠይቅ ቆይቷል።
በአገው ሕዝብ ዘንድ ፈረስ የዕለት ተዕለት ሕይወት አካልና ትልቅ ክብር የሚሰጠው እንስሳ ነው። ከጥንት ጀምሮ ለግብርና፣ ለሰርግ፣ ለለቅሶና ለተለያዩ ማህበራዊ ድግሶች በዋናነት ጥቅም ላይ ይውላል። ይህንኑ ጥብቅ ቁርኝት ለማስታወስም በ1933 ዓ.ም የተመሰረተው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዘንድሮ 86ኛ ዓመቱን ይዟል። ይህ በዓል ዕድሜ፣ ጾታና ሃይማኖት ሳይለይ በመላው ማህበረሰብ ዘንድ በድምቀት የሚከበር መሆኑም ተገልጿል።
አቶ መልካሙ አክለውም ለዚህ የምዝገባ ሂደት ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት የቅርስ ባለሥልጣን፣ የቢሮው ባለሙያዎችና አመራሮች፣ እንዲሁም የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ፕሬዝዳንት ምስጋና አቅርበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ የታሪክና የብዝሃ ሕይወት መገኛ መሆኗን ገልጸዋል። እነዚህን ፀጋዎች በአግባቡ መዝግቦና ጠብቆ ለዓለም በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት እንደሚገባም አሳስበዋል።
“ለአንድ ሀገር በየሁለት ዓመቱ አንድ ጊዜ በሚሰጠው ዕድል፣ የሕዝባችን የዘመናት ጥያቄ ለሆነው የአገው ፈረስ ባህል ምዝገባ ምላሽ ለማግኘት መቃረባችን ትልቅ ዕድል ነው” ያሉት ዶ/ር አህመዲን፣ የምዝገባው ቅድመ ሁኔታ ግማሽ መንገድ ላይ መድረሱን አብስረዋል።
የአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው፤ የአገው ሕዝብ ማንነቱንና አብሮነቱን ጠብቆ በመቆየቱ ዛሬ የድካሙን ፍሬ ለማየት መቃረቡን ገልጸው፣ ለመላው ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ቴዎድሮስ አክለውም፤ “ፈረስ ሲታሰብ የአድዋ ድል ቀድሞ ይነግሳል። ለነፃነታችን መሠረት ለጣለው የጥቁር ሕዝቦች ድል ፈረስ የፊት ተሰላፊ ባለውለታ ነበር። የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ፅንሰትም ከዚህ ኩሩ ታሪክ ጋር የተቆራኘ ነው” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ62 ሺህ በላይ አባላት ያሉት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር፣ 86ኛ ዓመቱን ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም በእንጅባራ ከተማ በድምቀት ለማክበር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል።
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር)፣ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር )፣ አቶ መልካሙ ጸጋዬ፣ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አባላትና ሌሎችም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
