የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ የሚካሄዱትን የአፍሪካ ህብረት 39ኛው የመሪዎች ጉባዔ እና 48ኛው መደበኛ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባዎችን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፣ የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ/ም 48ኛው መደበኛ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትሮች ስብሰባ በአፍሪካ ህብረት ይካሄዳል ብለዋል።
እንዲሁም የካቲት 7 እና 8 ደግሞ 39ኛው የመሪዎች ጉባዔ ይካሄል ሲሉ አሳውቀዋል።
በተያያዘ፣ ከዚህ ጉባዔ ጎን ለጎን የካቲት 6/2018 ዓ/ም የአፍሪካ እና ጣሊያን ጉባዔ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ መሪ ሀሳብ፣ ” ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት ” የሚል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ የመሪዎች ጉባዔ የባህር በር የማግኘት መብቷን እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ስላላት አቋም ለዲፕሎማቶች የምታንጸባርቅ መሆኑም ተገልጿል።
