የአፍሪካ ትልቁ ጠላት ውጫዊ አይደለም – የኢትዮጵያም!

Date:

በክቡር ገና (የምጣኔ ሀብት ምሁር )

የአፍሪካ ትልቁ ችግር ሌሎች የፈጠሩት ነውን? ብለን እንጠይቅ፡፡ አፍሪካ ለራሷ ለአፍሪካ ህልውና መከወን ተስኗት ይሆን? ብለንም ጠጠር ያለ መጠይቅ እናቅብ፡፡

የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጡ ከ60 አመታት በኋላ ይህን ጥያቄ ማንሳት ምቾት ይነሳ ይሆናል፡፡ የአፍሪካ ሀገሮች የራሳቸው ባንዲራ፣ መንግስታት፣ ህገ መንግስት፣ ብሄራዊ ባንክና በአለም አቀፍ ጠቋማት የራሳቸው መቀመጫ አላቸው፡፡

በራስ መተማመን መንፈስ ስለ አፍረካ ሀገሮች ሎአላዊነት፣ ስለ አፍሪካ ችግሮች አፍረካዊ መፍትሄዎችና ስለ አፍሪካ ተሀድሶ እናወራለን፡፡ ሆኖም ግን ከአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካዊ መዋቅር ስር ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ስናይ የቀድሞ የኢኮኖሚ መዋቅር በሚያስገርም መልኩ እንደነበር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ትላንት አፍሪካ ቡና፣ ካካዋ፣ ጥጥና ወርቅ ወደ ውጪ ትልክ ነበር፡፡ ዛሬ ድፍድፍ ዘይት፣ ኮባልትና መዳብ እየላከች ነው፡፡ ነገ ደግሞ ለአደጉት አገራት የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ አብዮት ግብአት የሚሆን ሊትየም፣ ገራፋይትና ሌሎች ጠቃሚ ማእድናትን ትልክ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ አፍሪካ ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት እንዳልወጣች ልብ ይሏል፡፡

በአለም አቀፍ የስራ ክፍፍል የአፍሪካ ይዞታ በበቂ ሁኔታ ተለውጣል? ብለን ስንጠይቅ በተፈጥሮ ያገኘነውን ወደ ውጭ ልከን የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት የሆኑትን ማሽኖችን፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን፣ የአህምሯዊ ሀብት ውጤት የሆኑትን ቴክኖሎጂዎችን፣ የተራቀቁ የፋይናንስ አገልግሎቶችንና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን እያስገባን መሆኑ እሙን ነው፡፡

በእርግጥ የአፍሪካ ከተሞች፣ መሰረተ ልማቶች፣ ትምህርት፣ የቴሌኮም አውታሮች፣ የፋይናንስ ስርአትና የማምረት አቅም ከቅኝ ግዛትነት በታላቀቀች ወቅት እንደነበረው አይደለም፡፡ እድገት እንዳለ አያጠያይቅም፡፡ እድገት አለ ማለት ግን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ተመዝግቧል ማለት አይደለም፡፡

እዚህ ላይ መሰረት ያለው ጥያቄ እናንሳ፡፡ አፍሪካ በአለም ኢኮኖሚ ያላትን ይዞታ ቀይራለች ወይስ የአስተዳዳር ስርአቷን ብቻ ነው ያሻሻለችው? ለምንስ ብለው ሌሎች አፍሪካን ለኛ ሲሉ ያበለጽጋሉ? እዚህ ላይ ቁርጡን መነጋጋር አለብን፡፡ የበለጸጉ ሀገራት ስለአፍሪካ ተጨንቀው የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሽግግር እውን ያደርጋሉ የሚለውን አደንዛዥ ቅዠት እርግፍ አድርገን መተው አለብን፡፡

አሜሪካ የአሜሪካ ቴክኖሎጂ በመሪነት አንዲዘልቅ ከለላ ትሰጣለች፡፡ አውሮፓ ለውሮፓ እንዱስቱሪዎችና የስራ ዕድል ከለላ ትሰጣለች፡፡ ቻይና የቻይና የምርት ሰንሰለትና ገበያ ተጠብቆ እንዲቆይ ከለላ ትሰጣለች፡፡ ጃፓን ለጃፓን ቴክኖሎጂ አቅም መጠናከር ከለላ ትሰጣለች፡፡

እነዚህ ሀገሮች ለስትራቴጂያዊ ጥቅማቸው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ድጎማ ያደርጋሉ፣ አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ያወጣሉ፣ የውጭ ንግድን ፋይናንስ ያደርጋሉ እንዲሁም ሁለንተናዊ ከለላ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ሴራ ወይም አሻጥር ሳይሆን መንግስታዊ የኢኮኖሚ አመራራ ጥበብ ነው፡፡

ስህተቱ የማንም ሳይሆን የራሳችን ነው፡፡ ስህተቱ ከነዚህና ከሌሎች የበለጸጉ ሀገራ ጋር የምናደርገውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንደ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር አድርገን መተርጎማችን ነው፡፡

አውሮፓውያን የአፍሪካን ወሳኝ የማእድን ምርቶችን ይፈልጋሉ ማለት አውሮፓውያን በአፍሪካ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ፋብሪካ እንዲገነባ ይፈልጋሉ ማለት አይደለም፡፡ የውጭ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመድሀኒት አምራቾች የአፍሪካን ገበያ ይፈልጋሉ ማለት አፍሪካውያን የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመድሀኒት ሎአላዊነታቸውን እንዲያረጋጋጡ አላፊነት አለባቸው ማለት አይደለም፡፡

አለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት የአፍሪካ ኢኮኖሚ የተረጋጋ እንዲሆን የሚፈልጉት ሀገራት የተበደሩትን መመለስ እንዲችሉ እንጂ አፍሪካ የኢንዱስትር አቅሟ እንዲጎለበት ሀላፊነት ስላለበቻው አይደለም፡፡ የበለጸጉ ሀገራት መንግስታት ተጠያቂነታቸው ለህዝባቸው ሲሆን ካምፓኒዎቻቻው ደግሞ ለባለአክሲዎኖቻቸው ነው፡፡

የበለጸጉት ሀገራትና ካምፓኒዎቻቻው ለጥቅማቸው መስራታቸው ነውር የለውም፡፡ ነውሩና አሳፋሪው ተግባር አፍሪካ ለአፍሪካ ጥቅም መስራት አለመቻሏ ነው፡፡

ይህ ሲባል ግን አፍሪካ ከበለጸጉ ሀገራ ጋር ኢኮኖሚያዊና የልማት ትብብር አታድርግ ማለት አይደለም፡፡ የውጭ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ትልቅ አስተዋትኦ አለው፡፡ አፍሪካ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ ገበያ፣ የመሰረተ ልማት ፋይናንስ እንዲሁም የእውቀት ሽግግር ያስፈልጋታል፡፡ ነገር ግን የልማት ድጋፍ የኢኮኖሚ ሽግግር እንዳልሆነ ልናጤን ይገባል፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሊሆን አይችልም፤ የሌሎች ስትራቴጂካዊ ጥቅምም የግድ የኛ ጥቅም ሊሆን አይችልም፡፡

ውጤትን የምንለካበትም የራሳችን መስፈሪያ ሊኖረን ይገባል፡፡ አንድ ሚኒሰትር ከውጭ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር አግኝቶ ሲመለስ፣ በአንድ ኢንቨስትመንት ጉባኤ የቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ቃል ሲገባ፣ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት በፍጥነት ሲያድግ እንደ ስኬት እምንቆጥር ከሆነ ነገር እንስታለን፡፡

ይልቅስ ጠጠር ያሉ ጥያቆችን ለመጠየቅና ጥቄዎቹንም ለመመለስ መድፈር ይጠበቅብናል፡፡ ከአስር አመታታ በፊት የማናመርታቸው አሁን ግን የምናመርታቸው ምንድናቸው? የአፍካውያን ካምፓኒዎች በየትኞቹ ቴክኖሎጂዎች ተራቀዋል? የትኛው የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ከመገጣጠም አልፎ በራሱ ዲዛይን የትኞቹን የኢንዱስት ምርቶች ለገበያ ያቀርባል?

የትኛውን ምርት በጥሬው ወደ ውጭ ከመላክ እሴት ጭምረን መላክ ጀምረናል? የትኛው የአፍሪካ ካምፓኒ በአለም አቀፍ ደረጃ በምርታማነትና በፈጠራ ተወዳዳሪ ሆኗል? ከዚህ ቀደም ከውጭ ከምናስመጣቸው ማሺነሪዎች ውስጥ ምን ያህሉን በራሳችን ማምረት ጀምረናል? የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅና ምላሽ መስጠት ይኖርብናል፡፡

እነዚህን ጥቄዎች መመለስ አመታዊ ጠቅላላ ምርት አብዛኛውን ጊዜ ሊመልሰው የማይችለውን የምርት አቅምን ሁኔታን ለማብራራትና በአግባቡ ለመመለስ ያስችላል፡፡ የማምረት አቅምን በብድር ገንዘብ ማገዝ ይቻላል፣ የውጭ ካፒታል የማማረት አቅምን ሊያፋጥን ይችላል፣ ንግድ ሊያጠናክረው ይችላል፣ እርዳታ ሊደግፈው ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን የማምረት አቅምን አይተኩም፡፡

አዲስ የማረት አቅምን ለመገንባት በማያስችል መልኩ በተደጋጋሚ የሚበደረውን ገንዘብ ለፍጆታ የሚያውል ኢኮኖሚ እድገትና ልማት አያስመዘግብም፡፡ ይልቁንም ይህን መሰል ኢኮኖሚ የነገን ጥገኘነትን ነው የሚያዋልደው፡፡ እናም የሁሉም ችግሮች ምንጭ ቅኝ ግዛት፣ ያልተመጣጠነ ንግድ፣ ድንበር ዘለል ካምፓኒዎች፣ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና ምእራባውያን መንግስታት ናቸው ብሎ ማላከክ ለጊዜው ይቻል ይሆናል፡፡ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቁ ከ60 አመታታ በኋላ ግን ይህ ተረክ ውሀ አያነሳም፡፡

እርግጥ ነው አለም አቀፉ ስርአት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የሀገር ውስጥ ፖለቲካ – ኢኮኖሚውም በፍትሀዊነት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ሸቀጦችን ወደ ውጪ የሚልኩ የተወሰኑ ሸቀጦችን ብቻ በመላክ አትራፊ ናቸው፡፡ ሸቀጦችን ወደ ሀገር የሚያስገቡም ከውጭ ሸቀጦች ጥገኝነት አትራፊ ናቸው፡፡ ከከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮችና ባለስልጣናት ጋር ቀረቤታ ያላቸውም ነጋዴዎች በተለየ ሁኔታ አትራፊዎች ናቸው፡፡

ባለስልጣናት የንግድና የስራ ፈቃድ፣ መሬት፣ የስራ ጨረታና የውጭ ምንዛሪን በመቆጣጠር ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደርና ሀብት ማጋበስ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ለሂቃንና ባለስልጣናት ይህ ልዩ ጥቅም ስለሚያማልላቸው ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር አይተጉም፡፡ ይህ ሁኔታ ከጥቃቅን ስርቆትና ሙስና ይልቅ ሀገርንና ህዘብን ለከፍተኛ ጉዳት ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ችግር ሙሉ በሙሉ ውጫዊ፣ ሙሉ በሙሉ ደግሞ ውስጣዊ ነው ብሎ መደምደም ያዳግታል፡፡ ለችግሩ መፈጠር ሁለቱም ማለትም ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ይመጋገባሉ፡፡ ለዚህም ነው በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር እጅግ አዳጋች የሆነው፡፡

ሌላው የአፍሪካ ችግር በ54 አገራት የተከፋፈለ የህግ ስርአት፣ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂና የድርድር ማእቀፍ መኖሩ ነው፡፡ እነዚህ ትንንሽ ገበያዎች ለየብቻቻው በአህጉር ደረጃ ከሚንቀሳቀሱና የኢኮኖሚ አቅም ካላቸው አለም አቀፍ ካፓኒዎች ጋር ስለሚነጋጋሩ የመደራደር አቅማቸው ደካማ አንደሚሆን እሙን ነው፡፡

በአፍሪካ ሀገራት መካከል የተቀላጠፈ የምርት ግብአትና የሸቀጦች ዝውውር አዳጋች ስለሆነ አለም አቀፍ ካምፓኒዎች በአፍረካ ውስጥ ላሏቸው እንደ አውቶ ሞቢል ላሉ ፋብሪካዎቻቻው ግብአት ከአፍሪካ ሀገራት ይልቅ ከውጭ ሀገራት ማስመጣት ይቀላቸዋል፡፡

ለምሳሌ አፍሪካ አቀፍ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመድሀኒት ምርት ካምፓኒዎችና የተለያዩ አህጉር አቀፍ ኢንዱስትዎች ያላደጉት በየሀገሩ የተለያዩ ፖሊሲዎች ደንቦችና መመሪያዎች በመኖራቸው ነው፡፡ ለዚህም ነው ባለፉት ጥቂት አመታት የተመሰረተው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በአፍሪካ ቀድሞ ይመረቱ የነበሩ ምርቶችን ግብይ ማገበያየት ብቻ ሳይሆን ከዚያ ሰፋ ያለና አዳዲስ ምርቶች እንዲመረቱና በስፋትም ግብይት አንዲፈጸም መትጋት የሚጠበቅበት፡፡

በአፍሪካ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር እውን አንዲሆን በአህጉር ደረጃ የሚንቀሳቀስ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመድሀኒቶች ምርትና የግብይት ሰንሰለት፣ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ፍብሪካ፣ የግብርና ምርት ማቀነባባሪያ፣ ክፍለ አህጉራዊ የኢንጂነሪንግ ማእከላት፣ የአፍሪካን እድገት የሚያፋጥኑ የፋይናንስ አገልግሎት ተቋማትን እውን በማድረግ በ54 ሀገራት ተከፋፋሎ ያለው 1.4 ቢሊዮን የአፍሪካ ህዝብ የጋራ ገበያ ተጠቃሚ ለማድረግ ራእይ መሰነቅና ተግባራዊ ማድረግም ይበቅብናል፡፡

የከፋው ችግር ደግሞ በአፍሪካ ሀገሮች ክፍፍል ብቻ አያበቃም፡፡ 54ቱም ሀገራት በውስጣቸው በብሄረሰብ፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት ተከፋፋለው በአንድ ሀገር ውስጥ የተከፋፈለ የፖለቲካ አመለካካት ማራመዳቸው ነው፡፡ በአንድ ሀገር የተለያየ ማንነት ወይም ብሄር ቤሄረሰብ መኖሩ በራሱ ችግር አይደለም፡፡

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን፣ ሀይማኖታቸውንና ታሪካቸውን መጠበቅና ማበልጸግ መብታቸው ነው፡፡ ችግሩ የሚመጣው እነዚህን ማህበረሰባዊ መብቶች ሽፋን በማድረግ ፖለቲካ ስልጣንን መያዝና ኢኮኖሚውን ለብቻ በበላይነት መቆጣጠር ነው መዘዝ ያለው፡፡

በአፍሪካ መንግስት መሬትን፣የስራ እድሎችን፣ ጨረታዎችን፣ የውጭ ምንዛሪንና ሌሎች እድሎችን ሁሉ ይቆጣጠራል፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ማጣት የነዚህን እድሎች ሁሉ ቁጥጥር ማጣት ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ስለዚህም የፖለቲካ ስልጣን በአፍሪካ የሞትና ሽረት ጉዳይ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ስልጣኑን ለመቆጣጠር ደግሞ በማንነት መሰባሰብ አዋጭና አትራፊ አካሄድ ሆኗል፡፡

በአፍሪካ የንግድ ስራዎች በፖለቲከኞች ይጠበቃሉ ይደገፋሉ፡፡ ወጣቶች በስራ ፈጠራ ከማመን ይልቅ በፖለቲከኞች ክንድ ይተማመናሉ፡፡ በጭሩ መንግስትን መጠጋት ከመባረክ ይቆጠራል፡፡ ኢኮኖሚያዊ መቀንጨር የማንነት ፖለቲካ እንዲፋፋ በር ከፋች ሲሆን ይህም በሂደት ተቋማዊ ልምሻን ያስከትላል፡፡

ለአፍካውያን የማንነት ፖለቲካን እንዲተው መንገር ችግሩን መለስተኛ ችግር ያስመስለዋል፡፡ ከዚያም ይልቅ አፍሪካውያን መንግስትን በእኩል ደረጃ የሁሉም ዜጋ ማድግ እንዳለባቸው አበክረን ልንታገል ይገባናል፡፡ መልካም እድሎች፣ የኑሮ መሻሻል፣ እድገትና ብልጽግና ከፖለቲካ ስልጣን ጥገኝነት ሊላቀቁ ይገባል፡፡ በምርጫ መሸነፍ የአለም መጨረሻ ያለሞኑንም ልብ ይሏል፡፡ የፖለቲካ ስልጣንን ከኢኮኖሚ ቁጥጥርና የበላይነት ጋር ማፋታት ለአፍሪካ መዳኛ ፍቱን መድሀኒት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሁኔታ ይህን ከላይ የተገለጸውን ምስል ቀልጭ አድረጎ የሚያሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሀይል አቅርቦት፣ በግብርና ሀብት፣ በስራ ፈጠራ አቅም፣ በስትራቴጂካዊ መልክአምድር፣ በትልቅ የሀገር ወስጥ ገበያና የበርካታ ወጣቶች ሀገር በመሆኗ እድሎችና ተስፈዎች አላት፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛው ፖለቲካዊ አቅሟ በማንነት፣ በታሪክ፣ በአስተዳደራዊ ድንበር፣ በፌዴራላ አደረጃጃት ጉዳዮችና መንግስትን ማን ይቆጣጠር በሚሉ ውዝግቦች በመባከኑ ወደፊት መራመድ አልቻለችም፡፡

ውዝግቦቹ ያሉ፣ የነበሩና ወደፊም የሚኖሩ ሆነው ሳሉ ስላላፈው በመጨቃጨቅ ምን ያህል ትውልድ ወርቃማ ጊዜውን ሲያባክን ይኖራል? ትርክቶችን እየተከተሉ አንዱ ሌላውን በጠላትነት ከሚመለከት ለምንድነው የወደፊት የጋራ እጣፈንታችንን መመልክት ያቃተን? ኢትዮጵያ በማንነት ላይ ስትጨቃጨቅ ሌሎች ሰው ስራሽ አስተወሎት ላይ እተወያዩ ነው፡፡ እኛ በአስተዳዳራዊ ድንብር ስንጨቃጨቅ ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ስለማጎልበት ይወያያሉ፡፡ የፖለቲካ ግጭት ጣማቂዎች ታሪክን እያጣቀሱ ማህበረሰቦችን ሲያቀሳስሩ ሌሎች በስራ ፈጠራ እየተመሩ የነገ ህይወታቸውን ያሳምራሉ፡፡

እንደ ሀገር እምንፎካከረው ኢትዮጵን ለመገንባት ነው ውይስ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ነው? ስንል መጠየቅ አለብን፡፡ እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ሲነሱ ብዘሀነትን ለመደፍጠጥ የታቀደ ሲራ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የጋራ ሀገር መገንባት ሲባል ግን ስለዜጎች የጋራ ተስፋ፣ ስለሁል አቀፍ ተቋማት፣ ስለ ህገ መንግስታዊ መብቶች ከፖለቲካ ተጽእኖ ውጪ ስለሚረጋጋጠው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህም የቀጣዩ ትውልድ ጥያቄ እኛ ማን ነን ከሚል ይልቅ በጋራ ምን ልንገነባ እንችላለን ወደሚል ተቀይሮ ለማየት የሁላችንንም ጥረት ይጠይቃል፡፡

በዚህ ዘመን እድገትንና ልማትን በተመለከተ ስለተነጻጻሪ ጥቅም በስፋት ይነሳል፡፡ የኢትዮጵያ ተነጻጻሪ ጥቅም የቡና ምርት ከሆነ የልጅ ልጆቻቻንም ቡና እየመረቱ ያቅርቡ ማለት ነው? ተነጻጻሪ ጥቅም የሚያመለክተው አንድ ሀገር በአንድ ተጨባች ሁኔታ ተወዳሪ ምርት ማምረት መቻሏን የሚያመለከት ነው፡፡

እንደየወቅቱ የልማት አመን ይህ ሁኔታ ይቀያየራል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ የተለያዩ ማሺነሪዎችና የኤሌክተሮኒስ እቃዎችን ለማምረት የሚያስችላት የጥሬ እቃ ተነጻጻሪ ጥቅም አልነበራትም፡፡ ሀገሮች በኢንቨስትመንት፣ እውቀት በመቅሰም፣ በከለላ፣ በኢንጂነሪንግ ልህቀት፣ በውጤታማ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ የማምረት አቅማቸውን ማጎልበት ይችላሉ፡፡ አፍሪካም ማድረግ ያለባት ይህንን ነው፡፡

አፍሪካን አሜሪካ፣ ቤልጂየም፣ ቻይና፣ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ወይም የአለም ባንክ ሊያሳድጓት አይችሉም፡፡ ለእድገቷ ግን አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ሽግግር ባለቤት ሊሆኑ ግን አይችሉም፡፡ ይህ ሀላፊነት የአፍሪካውያን ብቻ ነው፡፡ ሎአላዊነት የሚባለውም ይህ አንጂ ብሄራ ባዲራ ማውለብልብ ብቻ አይደለም፡፡ ሎአላዊነት የሚስማማውን መምረጥ መቻል ነው፡፡

በመሆኑም አፍሪካ ከምዕራቡና ከምስራቁ ጎራ አንዱን የመምረጥ ግዴታ የለባትም፡፡ አፍሪካ መምረጥ ያለባት አፍሪካን ነው፡፡ ከሁሉም ጋር መተባባርና የአንዱ ጥገኛ ያለመሆን አካሄድን መምረጥ ይኖርባታል፡፡ አስፈላጊ ሲሆን ለኢንዱስትሪዎቿ ከለላ መስጠት፣ አፍረካዊ ተቋማትን መገንባት፣ አግባብነት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ገበያዎችን ማቀናጀትና የመሳሰሉትን ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባታል፡፡ አፍሪካውያን ትላንት ከሌሎች ይገዙ የነበሩትን ዛሬ ማምረት ከቻሉ ይህ እድገት ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል የአፍሪካ ታለቁ ጠላት እንዲሁም የኢትዮጵያ ውጪያዊ አይደለም፡፡ አለም አቀፍ ሀይሎች ወደፊትም ጥቅማቸውን ማሳደዳቸው አይቀርም፣ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ለትርፍ መስራታቸውን ይቀጥላሉ፣ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተጽዕኗቻን ማሰረፋቸውን አይተዉም፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተፈጥሮ ማእድናትንና ለም መሬትን ብቻ በመያዥ አይዘለቅም፡፡ ይልቁንም በዚህ ዘመን በአሸናፊነት ለመዝለቅ እውቀትን ከማምረት አቅም ጋር አዋህዶ ተግባረዊ የሚያደርግን ምህበረሰብን መገንባት ይጠይቃል፡፡

አፍሪካ የተፈጥሮና የሰው ሀብት አላት፡፡ ጥያቄው አፍሪካ አቅሟን ለመጠቀም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አላት ? የሚል ይሆናል፡፡

አቶ ክቡር ገና ታዋቂ የምጣኔ ሀብት ምሁር ናቸዉ። በሀገራችን ኢኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያሉ መጣጥፎችን በማስነበብ እና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አስተያየቶችን በመስጠት ይታወቃሉ ። ይህን ፁሑፍ በግዮን መጽሔትና በማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዲወጣ አድርሰዉናል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ግዮን መጽሔት ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 9 2019 ዓ.ም ገበያ ላይ ውሏል !!!

-የግዮን እንግዳ አምዳችን :- ‹‹ምንጩና ጸሐፊው በማይታወቅ መረጃ መመራት አደገኛ...

ሸኽ መሃመድ አል አሙዲ ተጨማሪ 40 ሺህ ሠራተኞች እንዲቀጠሩ አቅጣጫ ሰጡ

የMIDROC Investment Group ሊቀመንበር ሼክ መሃመድ ሁሴን አል...

የወርቅ ማዕድን ሠራተኛው ከመገደላቸው በፊት ቤተሰባቸው ከታጣቂዎች ጋር ያደረገው የመጨረሻው የስልክ ምልልስ

ማስጠንቀቂያ፡ ቀጥሎ የሚያነብቡት ታሪክ ሊረብሽዎት ይችላል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ...