የአዲስ አበባ ስራ እና ክህሎት ቢሮ በመዲናይቱ ከህገወጥ አስራር ጋር በተያያዘ የሀገር ዉስጥ የስራ እና አሰሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ቁጥጥር እያደረገ ቢገኝም በህገወጥ መንገድ ተከፍተዉ የሚሰሩ ኤጀንሲዎች አሁንም መኖራቸዉን ለኢትዩ ኤፌ ኤም ተናግሯል።
የቢሮዉ የሀገር ዉስጥ የስራ ስምሪት ፍቃድ ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ በላይ ተሰማ አሁን ላይ በአዲስ አበባ 2መቶ 36 የሀገር ዉስጥ የግል ስራ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ህጋዊ አሰራር ዉስጥ እንደሚገኙ ነግረዉናል።
በሌላ በኩል በህገወጥ መንገድ ሲሰሩ የነበሩ እና የአሰራር ክፍተት የነበረባቸዉን 1መቶ 40 ኤጀንሲዎች ተጣርተዉ ንግድ ፍቃዳቸው እንዲታገድ ቢሮዉ ማድረጉን አቶ በላይ ገልፀዋል።
ከቢሮዉ ፍቃድ ሳይወስዱ እየሰሩ ካሉ ኤጀንሲዎች ጋር አንዳንድ አሰሪዎች እየሰሩ እንደሚስተዋል የነገሩን አቶ በላይ ቢሮዉ ንግድ ፍቃዳቸው እንዲታገድ እና ከፌደራል ፖሊስ ጋር እርምጃዎች እንዲወሰድ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የስራ እና ሰራተኛን ለሚያገናኙ ኤጀንሲዎች የብቃት ማረጋገጫ መስጠት እና ከስራ ሁኔታ ጋር የተያያዘ አቤቱታ እንዲሁም ቅሬታን እየተቀበለ መሆኑን ቢሮዉ ገልፆል።
አቶ በላይ ቀጣሪ ተቋማት ሰራተኞችን ከኤጀንሲዎች በሚቀጥሩበት ወቅት አስፈላጊውን ማጣራት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
