በባልና ሚስት መካከል በተፈጠረ ጊዜያዊ አለመግባባት ምክንያት የገዛ ልጁን በአንካሴ ወግቶ ለሞት ያበቃው አባት በ15 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱ ተገለጸ።
በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የተፈጸመው ይህ አሳዛኝ ወንጀል፣ በቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረን አለመግባባት በአመጽ ለመፍታት መሞከር የሚያስከትለውን ከባድ ውጤት የሚያሳይ ሆኗል።
በቦንጋ ከተማ አስተዳደር 01 ቀበሌ፣ ፏፏቴ በተባለው መንደር ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ ወንጀሉ መፈጸሙን የቦንጋ ከተማ ፖሊስ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ምርመራ የሥራ ሂደት አስተባባሪ ረዳት ኢንስፔክተር አራጋው አሰፋ ገልጸዋል።
በፖሊስ ምርመራ መሠረት፣ ባልና ሚስቱ በዕለቱ ገበያ ከዋሉ በኋላ ወደ መጠጥ ቤት በመግባት መጠጥ ሲጠጡ ቆይተው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል። በኋላም በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ተከሳሹ ባለቤቱን በያዘው አንካሴ ለመውጋት ጥቃት ፈጽሟል።
ሚስትየዋ ከጥቃቱ ለማምለጥ በመሮጥ ወደ ሌላ ሰው ቤት በመግባቷ ሕይወቷን ማትረፍ ችላለች። የወላጆቿን ጭቅጭቅ ሰምታ ወደ ውጭ የወጣችው ልጃቸው ግን በአባቷ ጥቃት ሰለባ ሆናለች።
ተከሳሹ ልጁን በአንካሴ ጭንቅላቷ ላይ በመውጋት ከባድ ጉዳት አድርሶባታል። ልጅቷም በማግስቱ በገብረፃዲቅ ሻዎ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላት ሳለ ሕይወቷ ማለፉን መርማሪው አስረድተዋል።
ሦስት የወንጀል ክሶች ቀረቡበት
የቦንጋ ከተማ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሕክምና ማስረጃዎች አጠናክሮ ለካፋ ዞን ፍትሕ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ አስረክቧል።
ዐቃቤ ሕግም ተከሳሹ በለጠ በላቸው ወ/ማርያም በሦስት የተለያዩ የወንጀል ክሶች እንዲጠየቅ ለካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦታል።
የመጀመሪያው ክስ በትዳር አጋሩ ላይ የግድያ ሙከራ መፈጸሙን የሚመለከት ሲሆን፣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 540 መሠረት ክስ ቀርቦበታል።
ሁለተኛው ክስ የገዛ ልጁን በአንካሴ ጭንቅላቷ ላይ በመውጋት ለሞት ያበቃ ጉዳት ማድረሱን የሚመለከት ሲሆን፣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 540 መሠረት የግድያ ክስ ቀርቦበታል።
ሦስተኛው ክስ ደግሞ ልጁ በአደጋ ላይ እያለች ሕይወቷን ለማዳን አስፈላጊውን እርዳታ አለማድረጉን የሚመለከት ሲሆን፣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 575 ንዑስ አንቀጽ 2(ሀ) መሠረት ክስ ተመስርቶበታል።
ፍርድ ቤቱ የ15 ዓመት ጽኑ እስራት ወሰነ
የካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግን ምስክሮች ቃልና የቀረቡለትን ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ፣ ተከሳሹ ክሱን ለማስተባበል ዕድል ቢሰጠውም ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ መሆኑን በመወሰን የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።
በዚሁ መሠረት ጥቅምት 26 ቀን 2019 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ ወንጀሉ ለሌሎች ማስጠንቀቂያ እንዲሆንና ተከሳሹንም ለማረም በሚል በለጠ በላቸው ወ/ማርያም በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።
ውሳኔውን የካፋ ዞን ዐቃቤ ሕግ ናትናኤል ክፍሌ መግለጻቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
