የትግራይ ክልል የፋይናንስ እና ሀብት ትብብር ቢሮ፤ የ8.5 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ክልሉን ለከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ እንዳዳረገው ገለጸ። ይህም የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ለመክፈል አዳጋች ከመሆኑም በላይ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ ማድረጉን ለኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር በላከው ይፋዊ ደብዳቤ አስታውቋል።
ቢሮው በደብዳቤው እንደገለጸው፤ ከጥቅምት እስከ መጋቢት ወር ድረስ ለክልሉ እንዲለቀቅ የሚጠበቀው ገንዘብ ባለመለቀቁ “መሠረታዊ የመንግሥት ሥራዎችን የሚያስተጓጉል አጣዳፊ የፋይናንስ ጫና” ፈጥሯል።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ምህረት በየነ ደብዳቤው መላኩን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠው፤ ይህም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የታገደው በጀት እንዲለቀቅ ቀደም ሲል ላቀረባቸው ተከታታይ ጥያቄዎች ምላሽ ባለመገኘቱ የተላከ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ወይዘሮ ምህረት ገለጻ፤ የፌዴራል መንግሥት ለቀረቡት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችም ሆነ ለቅርብ ጊዜው ይግባኝ እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።
የበጀት ጉድለቱ ያስከተላቸው ዋና ዋና ተጽዕኖዎች መካከል ከ141,000 በላይ ለሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መክፈል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፣ ለልማት ዓላማ ተመድቦ የነበረ 844 ሚሊዮን ብር ባለመለቀቁ በክልሉ የሚገኙ ከ20 በላይ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ተቋርጠዋል።
በ2018 የኢትዮጵያ በጀት ዓመት ለትግራይ 23.6 ቢሊዮን ብር የተመደበ ቢሆንም፤ እስከ መጋቢት ወር ድረስ መተላለፍ ከነበረበት 17.1 ቢሊዮን ብር ውስጥ ክልሉ ያገኘው 8.5 ቢሊዮን ብር ወይም ግማሹን ብቻ መሆኑ ተገልጿል።
የክልሉ ባለሥልጣናት የበጀት እጥረቱ ከጦርነት በኋላ እየተደረገ ያለውን የማገገም ጥረት፣ የመሠረታዊ አገልግሎት አቅርቦት እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን አስጠንቅቀዋል። ቢሮው የፌዴራል መንግሥት ቀሪውን ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲለቅ የጠየቀ ሲሆን፤ መዘግየቱ ከቀጠለ ቀውሱ ይበልጥ እየከፋ እንደሚሄድ ገልጿል።
ይህ የበጀት ውዝግብ ለወራት የቆየ ሲሆን፤ ባለፈው ታኅሣሥ ወር የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በጀት መዘግየቱ ደካማ የሆነውን ሰላም “ይበልጥ ደካማ” ሊያደርገው እንደሚችል ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ባለፈው ወር በትግራይ የሚገኙ መምህራን እና ተማሪዎች የፌዴራል መንግሥት የደመወዝ ድጋፍን አቋርጧል በሚል ተቃውሞ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ አዲሱ የፋይናንስ ቢሮ ደብዳቤም ቀውሱ መባባሱን የሚያረጋግጥ ሆኖ ተገኝቷል።
በህዳር 2018 ዓ.ም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባጋጠመው ከፍተኛ የበጀት እጥረት ምክንያት አዲሱን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ የደመወዝ ጭማሪ ሙሉ በሙሉ መተግበር አለመቻሉን የክልሉ ዕቅድ ኮሚሽን መግለፁን መዘገባችን ይታወሳል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ አዲሱን የፌዴራል የደመወዝ ስኬል ለመተግበር አሁን ከገጠመው ፈታኝ ሁኔታ በተጨማሪ እስካሁን ሳይከፈሉ የቆየ የሰራተኞች ክፍያን ችግርን ለመፍታት ትግል ላይ ይገኛል። በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሲቪል ሰራተኞች፣ ለመምህራን፣ ለጤና ሰራተኞች እና ለክልሉ ኃይሎች አባላት የሚከፈል ክፍያዎችን ለመሸፈን ከ20 ቢሊዮን ቢር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጾ ነበር። አስ
