19ኛው ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ። ጉባኤው የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓትን ለማሻሻል፣ ትብብርን ለማጠናከርና የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ሚና በማጉላት ውይይቶችን ያካሂዳል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ ጉባኤው ትስስርን ለመፍጠርና የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓትን በማሻሻል ለማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ ጠቃሚ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ በጋራ መሰባሰብና ገንቢ ውይይቶችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዘቡት ሚኒስትሯ፣ ጉባኤው በዓለም አቀፉ የጤና ዘርፍ አሠራርና መዋቅር ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት የጤና ሥርዓቱ መሠረታዊ አካል መሆኑን ያብራሩት ዶ/ር መቅደስ፣ ኢትዮጵያ ከማዕከላዊ አቅርቦት እስከ ታችኛው የማህበረሰብ ደረጃ ድረስ የሚደርስ ጠንካራ ሥርዓት እየገነባች መሆኑን አስታውቀዋል።
በአቅርቦት ሰንሰለት ፖሊሲ፣ በገበያ፣ በካፒታልና በተደራሽነት ዘርፎች ያላትን ልምድ ያካፈሉት ሚኒስትሯ፣ በሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት እድገትና ለዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት እድልም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት (EPSS) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ፣ ጉባኤው ለተቋሙ የልምድ ልውውጥና ተግዳሮቶቹን ለመፍታት አዲስ አቅጣጫ ለመፈለግ ጠቃሚ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በአቅርቦት ሰንሰለቱ የሚታዩ የፋይናንስ እጥረት፣ የአሠራር መበታተንና መድኃኒቶችን እስከ ታችኛው የማህበረሰብ ደረጃ ድረስ ለማድረስ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ዘርዝረዋል። በተጨማሪም የአፍሪካ የመድኃኒት አምራቾች የበለጠ ትኩረት እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዣን ካሴያ በበኩላቸው፣ በአፍሪካ የጤና አቅርቦት ሰንሰለትን ለማሻሻል የሚያስችል ፍኖተ ካርታ አቅርበዋል። በአፍሪካ ውስጥ የመድኃኒት ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማጠናከር ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን አመልክተዋል።
ጉባኤው በተለያዩ ውይይቶችና የልምድ ልውውጦች በመቀጠል፣ በጤና አቅርቦት ሰንሰለት ዘርፍ የትብብርና የማሻሻያ እድሎችን ይመለከታል።
