ኳታር ኢራን ሰኞ ዕለት በአሜሪካ አል ኡዲድ የጦር ሠፈር ላይ የፈጸመችውን ጥቃት በመኮነን ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ ደብዳቤ ጻፈች።
የኳታር ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለቻ ላይ ደብዳቤው ጥቃቱ የኳታር “ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት” ላይ የተፈጸመ “እጅግ አደገኛ እና ግልጽ ጥሰት” መሆኑን ገልጿል።
ደብዳቤው የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሚሳኤል ጥቃት “ለአካባቢው ሰላም እና ደህንነት ቀጥተኛ ስጋት” መደቀኑንም ያብራራል።
“የኳታር መንግሥት ከዚህ ግልጽ ጥቃት ተፈጥሮ እና መጠን ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ምላሽ የመስጠት መብቱ የተጠበቀ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል” ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።
የኳታር መንግሥት የኢራን አምባሳደርን ጠርቶ ማናገሩንም አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ሰኞ ዕለት በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሰፈር ላይ የተፈፀመውን የሚሳኤል ጥቃትን ሙሉ በሙሉ ማክሸፏን ገልጿል።
