የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2 በመቶ የነበረውን የመከላከያ ወጪ በ2035 ወደ 5 በመቶ ለማሳደግ መስማማታቸው ተገለፀ።
አባል ሀገራቱ ስምምነቱን የፈፀሙት በኔዘርላንድስ ሔግ በተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ ነው፡፡
በጉባኤው የ32ቱ አባል ሀገራት መሪዎች በ2035 ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸው አምስት በመቶ የሚሆነውን ለመከላከያ እና ደህንነት ለማዋል ቃል መግባታቸው ተነግሯል።
ማርክ ሩት የኔቶ ዋና ጸሐፊ ከሆኑ በኋላ የኔቶ አባል ሀገራት የመከላከያ ወጪን 5 በመቶ እንዲሆን ለ9 ወራት ሲሰሩ መቆየታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በጉባኤው ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔው “ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ እና ለምዕራቡ ስልጣኔ ትልቅ ድል ነው” ብለዋል።
የኔቶ ዋና ፀሃፊ ማርክ ሩት በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ሃገራት ለመከላከያ በጀት የበለጠ ሀላፊነት የሚወስዱበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
ድርጅቱ የሚያቀርበው የሰላም ጥሪ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና ፀሃፊው ጠቅሰዋል።
