በትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች እግድ ተጥሎባቸው የነበሩ ሶስት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን ከክልሉ ግዜያዊ አስተዳደር ጋር “በማቀራረብ እንዲስማሙና በጋራ እንዲሰሩ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሪያለሁ” ሲል የትግራይ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ፎረም አስታወቀ።
የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም ተሰብስበው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራውን ጊዜያዊ አስተዳደር ማውገዛቸውን ተከትሎ ተቃውሟቸውን በመግለጸ ስብሰባውን ረግጠው በወጡ አመራሮች ላይ እግድ መጣሉ ይታወሳል።
በሰራዊቱ አመራሮች እግድ ከተጣለባቸው መካከል ነበሩ የተባሉት ጄኔራል ጉኡሽ ገብሬ፣ ጀነራል ከበደ ፍቃዱ እና ኮሎኔል ገ/ዮሐንስ ዮሃንስ (የአባተ ልጅ) የተባሉ ወታደራዊ ሃላፊዎች ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋር እንዲስማሙና እንዲግባቡ በማድረግ አለመግባባቱ እንዲፈታ አድርጊያለሁ ሲል ፎረሙ በመግለጫው አስታውቋል፤ “በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በመለየት እንዲወያዩ እና በጋራ መስራት የሚያስችላቸው መድረክ እንዲፈጠር አስችያለሁ” ብሏል።
በተያዘው አመት 2017 ጥር ወር ላይ ራሳቸውን የትግራይ ኃይል አመራሮች ብለው የሚጠሩት የክልሉ መኮንኖች ለቀናት ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ጥር 15/2017 ዓ.ም. መቀለ ውስጥ በሰጡት መግለጫ በአቶ ጌታቸው ረዳ ይመራ የነበረው የጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደ አዲስ እንዲዋቀር ውሳኔ ማሳለፋቸውን መዘገቡ ይታወሳል።
በወቅቱ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም በማለት “የሌሎች መጠቀሚያ ሆኗል” የሚል ክስ አቅርበዋል።
አመራሮቹ ባወጡት መግለጫ በጊዜያዊ አስተዳደሩ “ቁልፍ ሥልጣን የነበራቸው አመራር እና አባላት ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ክህደት በመፈጸም የውጭ ኃይል መሣሪያ ሆነዋል” ብሏል።
በተጨማሪም አመራሮቹ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “ድክመቶች” ላይ የሚያተኩር እና አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየሞከረ ነው በማለት ወቅሰዋል።
በዚህም ምክንያት “የተዳከመ” እና “ተልዕኮውን የዘነጋ” ያለውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማጠናከር አመራሮቹ ተነስተው በሌሎች መተካት እንዳለባቸው አሳስቧል።
ፎረሙ ነሃሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በትግራይ ክልል ያጋጠመውን ሁሉን አቀፍ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሰራሁ ነው” ሲል አስታውቋል። በተለይም ደግሞ “የክልሉን ህዝብ ስጋት ውስጥ ያስገባውን የጸጥታ እና ውስጣዊ የፖለቲካ ችግር በሰላማዊና በውይይት እንዲፈታ ለማድረግ በትጋት እየሰራሁ ነው” ብሏል።
ቀደም ሲል “ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በትግራይ እና በፌዴራል መንግስት መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ የትግራይን ህዝብ መብት በማረጋገጥ ዙሪያ ተወያይተናል” ያለው ምክር ቤቱ “የሚጨበጥ ተስፋም ተገኝቷል” ብሏል።
“በውስጣችን ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ በቅርበት እየተመለከትን እና ይሆናል ያልነውን መፍትሄ ለማግኘት እየሞከርን ነው” ሲል ጠቁሟል።
በእግድ ላይ የነበሩ አዛዦች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር መቀራረባቸው እና እርቅ መፈጸማቸው “ሰላም ፈላጊ ህዝባችንን በመወከል ለሁሉም ያለንን ክብር እና ምስጋና እንገልፃለን” ብሏል፤ “እነዚህ ለህዝባቸውና ለክልላቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ የትግራይ ተወላጆች በአንድ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው የህዝባቸውን አገራዊ ዓላማ ለማስፈጸም በጋራ ለመስራት መስማማታቸው እንደ ተቋም እንዳስደሰተው” ምክር ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።
በክልሉ “የትግራይን ጥቅም የሚያስቀድም የፖለቲካ አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ልዩነቶች ሁሉ በድርድርና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፣ የክልሉ ህዝብ በአፋጣኝ ወደ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ትኩረት አድርጎ እንዲያገግም በሚያስችሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አጠናክሬ እሰራለሁ” ብሏል።
በ2017 ጥር ወር ላይ የትግራይ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ውሳኔ “ግልፅ መፈንቀለ መንግስትና የፕሪቶሪያውን ስምምነት አደጋ ላይ የጣለ ነው” ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ማጣጣሉን መዘገባችን ይታወሳል።
“መግለጫው ግልፅ የሆነ መፈንቀለ መንግስት ያወጀ እና የፕሪቶሪያውን ውል ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው” ሲል የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ህጋዊ ያልሆነ ቡድን ደግፎ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ለማፍረስ ፤ ስርዓት አልበኝነት ለማስፈን እና ሰራዊቱን ለመበተን መንቀሳቀስ ተቀባይነት የለውም” ሲል ገልጿል።
በሰራዊቱ አመራሮች እግድ ከተጣለባቸው መካከል አንዱ የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ገብረእግዚአብሄር በየነ፤ በአፋር እና በትግራይ ክልሎች ውስጥ “አራት ክፍለ ጦር” ያለው የራሳቸውን ሠራዊት ማደራጀታቸውን መናገራቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይተወሳል።
ከትግራይ ኃይሎች በመለየት የራሳቸውን ሠራዊት እየገነቡ መሆናቸውን የጠቀሱት ብርጋዴር ጄነራል ገብረእግዚአብሄር፤ “አዲስ ነገር ለመፍጠር” ወደ በረሃ መውደረዳቸውን እና “ከፓርቲ ነጻ የሆነ ኃይል ለመፍጠር፣… ፓርቲ የማያዝዘው ሠራዊት ለመፍጠር” እየተንቀሳቀሱ መሆኑን መግለጻቸውን ቢቢሲን ዋቢ በማድረግ በዘገባው ተካቷል።
ጄነራሉ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ከትግራይ ሠራዊት አመራሮች ጋር የተለያዩት ከጥር 15/20017 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ማስረዳታቸውም ይታወሳል። አስ
