የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ሃማስ ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅዱን እስከ ነገ እሁድ እንዲቀበል ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ፣ ቡድኑ ትላንት አርብ የሰላም ዕቅዱን እንደሚቀበልና ታጋቾችንም እንደሚለቅ አስታውቋል፡፡
ሃማስ የሰላም ዕቅዱን እንደሚቀበል ባስታወቀ በሰዓታት ውስጥም ትራምፕ እስራኤል ጋዛን መደብደብ እንድታቆም አሳስበዋል፡፡
ስፑትኒክ እንደዘገበው፤ እስራኤል የጋዛ ወረራ እንዲቆም ያዘዘች ሲሆን፤የእስራኤል መከላከያ በጋዛ የመከላከል እርምጃዎችን ብቻ እንደሚያከናውን ተጠቁሟል፡፡
ቴል አቪቭ ከሃማስ ቡድን ምላሽ በኋላ ሁሉንም ታጋቾች ለማስፈታት፣ የትራምፕን እቅድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ወዲያውኑ ተግባራዊ እያደረገች ነው ሲል የእስራኤል ጠ/ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ሃማስ ባወጣው መግለጫ ላይ በመመስረት ለዘላቂ ሰላም ዝግጁ መሆናቸውን አምናለሁ። ታጋቾቹን በሰላምና በፍጥነት ማውጣት እንድንችል እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርሰውን የቦምብ ጥቃት በአስቸኳይ ማቆም አለባት።
በአሁኑ ሰዓት ይህን ለማድረግ በጣም አደገኛ ነው። በዝርዝር ጉዳዮች ላይ እየተወያየንበት ነው፡፡ ይህ ስለ ጋዛ ብቻ አይደለም፤ ይህ በመካከለኛው ምስራቅ ለረዥም ጊዜ ሲፈለግ የቆየ የሰላም ጉዳይ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
