ትላንት ከረዥሙ እስሬ የተፈታሁበት ዐሥረኛ ዓመት መሆኑን ጋዜጠኛ ኤርምያስ በጋሻው አስታወሰኝ። ይህም ብዙ ትዝታ ቀሰቀሰብኝ። ዞን ዘጠኝ ጭቆና የወለደው ንቅናቄ ነበር። ስንመሠርተው የጀመርነው ነገር ክብደት በቅጡ አልገባንም ነበር (መሰለኝ)። በደመ ነፍስ ጭቆናን እምቢ በማለት ነበር የጀመርነው።
ሆኖም የዋህነታችን ለብዙዎች ስለተጋባባቸው አብረውን ቆሙና ንቅናቄው አደገ። ያኔ ፌስቡክ እንደዛሬው አላበደም። ስለዚህ በመጠኑም ቢሆን ሰከን እያሉ መነጋገር ይቻል ነበር። በዚህ መሐል መንግሥት ጋማችንን ይዞ ወህኒ ቤት ወረወረን። በ18 ወራት ውስጥ እየተንጠባጠብን ተፈታን። እኔ የመጨረሻው ተፈቺ ነበርኩ፤ ጥቅምት 11፣ 2008።
የተፈታሁ ዕለት አንገቴ ላይ የገዳ ባንዲራ በስካርፍ መልክ ጠምጥሜ ነበር። አንዲት ጓደኛዬ ከመፈታቴ ሳምንት ቀደም ብላ፣ ቢሾፍቱ ለኢሬቻ አከባበር ደርሳ ስትመለስ ልትጠይቀኝ መጣች። ያኔ ኢሬቻን ማክበር መንግሥትን ከመቃወም እኩል ስሜት ነበረው። ጓደኛዬ ስትመጣ የገዛችውን የገዳ ስካርፍ ለብሳ ነበር።
ስለ ባንዲራው አመጣጥ የዛን ሰሞን ተሰርቆ የገባልኝ መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩትን አወራሁላት። “ልስጥህ?” አለችኝ። “አዎ” አልኳት። ሰጠችኝ። ስወጣ እርሱን ለብሼ ወጣሁ። እንደ እውነቱ መልዕክት አለው ብዬ እምብዛም አላሰብኩበትም። ነገር ግን የኢትዮጵያ/አማራ ብሔርተኞች በጣም ተናደዱብኝ። እኛ በቻልነው አቅም ሁሉ ስንደግፈው እና ካምፔይን ስናረግለት ከርመን የኦሮሞ ብሔርተኞችን እያመሰገነ ወጣ የሚል አንድምታ ሰጡት።
በእስራችን ወቅት ሁሉም የሚያወድሰን ቅምጥሎች ነበርን። አዲሱ ዘመቻ ወዳጅ ዘመዶቻችንን በጣም አስደነገጠ። ጋዜጠኛ ዘካርያስ ዘላለም “Zone 9 Bloggers ‘guilty’ This Time!?” የሚል ረዥም መጣጥፍ ነገሩን በመታዘብ ጻፈ።
ግራ የገባኝ እኔ ለማገኘው ሰው ሁሉ ማብራሪያ እሰጥ ነበር። እንደውም በወንድሜ አካውንት በኩል ለሔኖክ የሺጥላ (እሱም ትችት ጽፎ ብዙ ሰው እንደወደደለት አስነብበውኝ) ማብራሪያ ላኩለት። የኦሕዴድና የገዳ ባንዲራ ይለያል፣ የገዳ ባንዲራ አመጣጥ ትውፊት እንዲህ፣ እንዲያ ነው፣ ምናምን አልኩት። እሱም በምስጋና ማብራሪያው ተመችቶኛል፣ እንዲያውም በፍቃዱ ከላከልኝ እኔም ለብሼው ፎቶ ተነስቼ እለጥፋለሁ አለ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሌላ ጓደኛዬ እንኳን ተፈታህ ልትለኝ ስትመጣ ስካርፍ በስጦታ ይዛልኝ መጣች። ለደጋፊዎቻችን ምስጋና ለማቅረብ የቡድን ፎቶ ስንነሳ አዲሱን ስካርፍ ለብሼ ተነሳሁ። አዲሱ ስካርፍ ጥለቱ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ነበር። አንዳንዶች ሕዝባዊ መሠረቴን ለመካስ ያደረግኩት እንደሆነ አሰቡልኝ። እውነቱን ለመናገር የዚህ ጊዜም እኔ በቅጡ አላሰብኩበትም ነበር።
ይህ አጋጣሚ ብዙ እንዳስብ ረድቶኛል። ከፌስቡክ ምርቃቶች ይልቅ እርግማኖች በጣም ጠቃሚ ናቸው። እንድናስብ ያስገድዱናል። ከዚያ በኋላ ብዙ አሳልፌያለሁ። በምጽፈው ሁሉ ተጠርጣሪ ነኝ። በተለይ አንድ ጊዜ በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያ የጻፍኩት ጽሑፍ ከጠበቅኩት በላይ አወዛገበ።
በኋላ ደግሞ በአማራ ብሔርተኝነት ላይ የጻፍኩት መጣጥፍ ከብዙ የፖለቲካ ወዳጆቼ አፋታኝ። ሁኔታው ለወዳጅ ዘመድ አስቸጋሪ ነው። በተተቸሁ ቁጥር የፖለቲካ አመለካከቴ የበለጠ እየተሳለ እና ከብዙኃኑ ጋር በአመለካከት እንደማልስማማ እየተገለጠልኝ መጣሁ። የኢትዮጵያ ብሔርተኛ እና የዳግማዊ ምኒልክ አድናቂ ሆኖ ላደገ ለኔ ዓይነቱ እንዲህ ዓይነቱ ኩርኩም አስፈላጊ ነው።
ቴዎድሮስ ፀጋዬ፣ የምወድለት ግጥም አለችው።
«የራስ ቅሉን በኩርኩም፥ ባደባልቀው እንደቃ፣
ፈጥኖ ባይመልስም ቅሉ፥ እያደረ ግን ነቃ።»
ነቃሁ። መንቃቴን ግን ብዙዎች ይስማሙበታል ማለት አይደለም። ያው መሠረቴ ተነቃነቀ።
ባለፉት ዐሥር ዓመታት ብዙ ከመሞረዴ የተነሳ የዛሬ ዐሥር ዓመት የጻፍኳቸው ጽሑፎች በትዝታ መልክ ሲመጡ እደነቃለሁ። በአለማወቄ ላይ ብዙ ድፍረት ሰጥቶኛል። ብዙ አጥፍቼያለሁ፣ ብዙ አልምቻለሁ። ዝም ብል ኖሮ ከስህተቴ የመማር፣ የማውቀውን የማሳደግ ዕድል አይኖረኝም ነበር።
ሒደቱ ግን በጣም አባጣ ጎርባጣ ነው። ብዙ ወዳጅ ሰጥቶኛል። ብዙ ወዳጅ ነጥቆኛል። አንዳንዴ የፖለቲካ አመለካከቴ ከወዳጅ ዘመዶቼ አንፃር የተቃረነ በመሆኑ እንዴት ችለውኝ ወዳጅነታቸውን ጠብቀው እንደኖሩ ይገርመኛል።
መለስ ብዬ ሳየው የባንዲራው ውዝግብ ያስገርመኛል። ዛሬ በደረስኩበት የፖለቲካ ብስለት (ብስለት አይደለም የሚል ካለም መብቱ ነው) ለየትኛውም ብሔረሰብ የተለየ ፍቅር ወይም ጥላቻ የለኝም፤ የትኞቹም ውስጥ ቦታ የለኝም። እንዲኖረኝም አልፈልግም። ለሁሉም ብሔርተኞችም እኩል ትዝብት ነው የማከፋፍለው።
ይህንን ስል የኢትዮጵያ ብሔርተኞችን ያስተረፍኩ የሚመስለው ይኖራል። ትዝብቴ እንዲያውም በነርሱ ሳይብስ አይቀርም። የባንዲራ ጉዳይንም ባሰብኩ ቁጥር ከብሔርተኝነት ጋር ነው የማዛምደው። ባጭሩ ከሁሉም ተፋትቻለሁ። እነዚያ ሁሉ ትችቶች ባያርፉብኝ ኖሮ አልለወጥም ነበር የሚለውን ሳስበው፣ ትችቶቹን እንዳመሰግናቸው ይረዳኛል። ነፍስ አሳውቀውኛል።
ቺርስ ለወዳጅነታችን፣ ችርስ ለትችቶቻችሁ 🥂
ከበፍቃዱ ዘ ሀይሉ
