በፍሎሪዳ ግዛት ፓልም ቢች በሚገኘው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማር-አ-ላጎ መኖሪያ ግቢ ውስጥ የተከለከለ የጥበቃ ክልል ጥሶ የገባ የ20 ዓመት ወጣት በጥይት ተመትቶ መገደሉን የአሜሪካ ሚስጥራዊ አገልግሎት አስታወቀ።
እንደ ሚስጥራዊ አገልግሎቱ መግለጫ ከሆነ ግለሰቡ በመኖሪያው ሰሜናዊ በር አካባቢ ያለውን የጥበቃ ክልል ጥሶ ሲገባ የታየ ሲሆን፣ በወቅቱ የአደን ጠመንጃ የሚመስል መሣሪያ እና የነዳጅ መያዣ ይዞ እንደነበር ተረጋግጧል።
በስፍራው የነበሩ የጸጥታ አካላት በወሰዱት አፋጣኝ እርምጃ ግለሰቡ በዚያው ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
በጥቃቱ ሙከራ ወቅት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በመኖሪያው ውስጥ አልነበሩም።
ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ዋይት ሀውስ ውስጥ እንደነበሩ ታውቋል።
በአሁኑ ሰዓት የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (FBI) ከሚስጥራዊ አገልግሎት እና ከአካባቢው ፖሊስ ጋር በመተባበር ስለ ግለሰቡ ማንነትና ስለ ጥቃቱ ዓላማ ጥልቅ ምርመራ እያደረገ ይገኛል።
ይህ ክስተት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ካጋጠሟቸው ተከታታይ የደህንነት ስጋቶች መካከል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
