በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚገኘዉ ሚሊኒየም አዳራሽን የማፍረስ ስራ ጀመረ

Date:

ባለፉት 18 ዓመታት በኢትዮጵያ ግዙፍ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች ሲያስተናግድ የቆየው ሚሊኒየም አዳራሽ፣ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለታቀደው ሰፊ የመልሶ ግንባታና የማስፋፊያ ስራ እንዲመች የማስፈረስ ሂደት መጀመሩን ካፒታል ጋዜጣ ተመልክቷል።

ይህ ታላቅ የአዳራሽ እድሳትና የማስፋፊያ ፕሮጀክት በዋናነት ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው 32ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ዝግጅት አካል ሲሆን፣ በቦታው ላይ Moxy by Marriott የተሰኘ ግዙፍና ዘመናዊ ሆቴል እንደሚገነባ ታውቋል።

በዚያስ አርክቴክቸር የተነደፈው ይህ የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ከመሬት በታች ሰፊ የመኪና ማቆሚያ፣ የላቀ ቴክኖሎጂ እና የተሻሻለ የእግረኞች ፍሰትን ያካተተ ሲሆን፣ የአዳራሹን የማስተናገድ አቅም እና ዘመናዊነት ይበልጥ በማሳደግ ተጨማሪ ጎብኚዎችን ለመሳብ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ቀደም ብለው እንደገለጹት፣ ግሩፑ ለ32ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተሳታፊዎች የሚሆኑ 1,500 አልጋዎችን የያዙ አምስት ዘመናዊ ሆቴሎችን በአዲስ አበባ ለመገንባት በከፍተኛ ርብርብ ላይ ይገኛል።

ከእነዚህም መካከል በሚሊኒየም አዳራሽ ቅጥር ግቢ የሚገነባው “Moxy by Marriott”፣ በመሀመድያ የመኖሪያ መንደር የሚገነባው “Four Points by Sheraton” እና በሸራተን አዲስ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገነባው ሌላ ተጨማሪ ዘመናዊ ሆቴል ተጠቃሽ ናቸው።

በተጨማሪም በቅርቡ ወደ ሚድሮክ ቤተሰብ የተቀላቀለው ዋቢሸበሌ ሆቴል በ “Autograph Collection by Marriott” ብራንድ ደረጃውን ጠብቆ ለጉባኤው ዝግጁ የሚሆን ሲሆን፣ በአፍሪካ ህብረት አጠገብ የሚገኘው “Westin Addis” ቀሪ ስራዎችም እየተጠናቀቁ ይገኛሉ።

ግሩፑ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞችም የሆቴል ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በዚሁ መሰረት በጂማ እና በሀዋሳ ከተሞች “Four Points by Sheraton” ሆቴሎች ግንባታ ላይ ሲሆኑ፣ በባህር ዳር ከተማ ደግሞ “Four Points by Sheraton” እና “Protea by Marriott” ሆቴሎችን ለመገንባት ዝግጅቱ መጠናቀቁ ታውቋል።

ከዚህም ባሻገር ሚድሮክ በቅርቡ የላንጋኖ ሳቫና ሪዞርትን በግዥ የተረከበ ሲሆን፣ ስፍራውን በማርዮት ብራንዶች ስር ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ በማሳደግ ወደ ስራ ለመግባት እቅድ መያዙን ካፒታል ለመረዳት ችሏል።

በ2000 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሚሊኒየም አከባበር ወቅት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ ግዙፍ አዳራሽ፣ በ20 ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈና በአንድ ጊዜ እስከ 25 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው የአገሪቱ ግንባር ቀደም መሰብሰቢያ ስፍራ ነው። ከታህሳስ 2018 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ሊፈር እንደሆነ ካፒታል ከዚህ ቀደም መዘገብ የሚታወስ ሲሆን አሁን ግን ከታቀደበት ወራት ዘግየት ብሎ የካቲት 2018 መጨረሻ ላይ ተጀምሯል።

በአዲስ መልኩ እንዲገነባ የተወሰነው ይህ አዳራሽ፣ ለግንባታው የሚወጣው የኢንቨስትመንት መጠንና የስራ ተቋራጩ ማንነት በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግ ተመላክቷል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አዳራሹ ካለው ታሪካዊ ፋይዳ ባሻገር ለዘመናዊ የከተማ ልማት እና ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ኩነቶች ምቹ የሆነ መሠረተ ልማት ሆኖ እንደሚያገለግል ታምኖበታል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...